
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ሰከላ ወረዳ ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኘው ክፍለ ጦር በአካባቢው ለዘረፋ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጽንፈኛው ቡድን አባላትን መያዙን አስታውቋል። በሰከላ ከተማ በመከላከያ ስም እና ማዕረግ ከኅብረተሰቡ ገንዘብና ስልኮችን በመስረቅ የሠራዊቱን ስም ለማጠልሸት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ግለሰቦችን ነው በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የገለጸው፡፡
የክፍለጦሩ አዛዥ ኮሎኔል ድባቤ አበራ ጽንፈኛው ሠራዊቱ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን መልካም ስም ለማጠልሸት እና ኅብረተሰቡ በሠራዊቱ ላይ ያለውን አመኔታ ለማኮሰስ በሠራዊቱ ስም እና ማዕረግ እንዲዘርፉ በከተሞች ግለሰቦችን መድቦ እየሠራ ነው ብለዋል። የክፍለጦሩ አዛዥ በሰከላ ከተማ ተሰማርተው በሠራዊቱ ስም እና ማዕረግ ከሕዝቡ ሲዘርፉ የነበሩ የጽንፈኛው ቡድን አባላት ዝና ትዛዙ ጡሩነህ፣ ዋለ ገረመው ወርቅነህ እና በለጠ ስመኝ እንየው እጅ ከፈንጅ ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
የጽንፈኛው ኀይል የመጨረሻው አማራጭ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው የቆየ የዘረፋ ልምዱን በሠራዊቱ ስም እና ማዕረግ በማድረግ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲጠላ እና የተቋሙን መልካም ስም ጥላሸት ለመቀባት ምርጫ የሌለው ዘዴው ነው ብለዋል። በቁጥጥር ስር የዋሉት የጽንፈኛው ተልዕኮ ፈፃሚዎች የአማራን ወጣት እያሠለጠኑ በማሰማራት፣ እገታ በመፈጸም ገንዘብ መቀበል፣ ኬላ ጥለው ከሕዝብ ትራንስፖርት መዝረፍ ቀዳሚ የገቢ ምንጫቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ይህንን የቆየ ልምዳቸውን ሊያተርፉበት መከላከያ በሚገኝበት አካባቢ የሠራዊቱን ማዕረግ እና ስም እየተጠቀሙ ገንዘብ መቀበል፣ በልቶ እና ጠጥቶ አለመክፈል፣ ኅብረተሰብ መደብደብ እና መሰል ተግባራት እንዲፈጽሙ ተልዕኮ ተቀብለው በየከተሞች ስለመሰማራታቸው ነው የተናገሩት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!