
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት ተመጽዋችነትን ማስቀረት የሚያስችል ሥራ በስፋት እየተከናወነ መኾኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል። የበጀት ዓመቱ የመጨረሻው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማው በማክሮ ኢኮኖሚ እና ዋና ዋና ዘርፎች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል። በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ፣ በሩዝ ልማት እና በአጠቃላይ ሰብል ልማት ከፍተኛ ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል። በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም እያንዳንዱ ቤተሰብ የተመጣጠነ የምግብ ሽፋንን እንዲችል እና የአመጋገብ ባሕሉን እንዲለውጥ የሚያደርግ ምዕራፍ መከፈቱን ነው የተናገሩት።
በምግብ እህል ራስን ለመቻል ኢኒሼቲቮችን ከመተግበር ባለፈ ከሕዝቡ ጋር መግባባት በመፍጠር ለልማት ቆርጦ እንዲነሳ በየክልሎች ሰፋፊ መድረኮች መከናወናቸውንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የተመጽዋችነት ታሪክ እንዲያበቃ ከታታሪው ሕዝብ ጋር በመኾን ያለውን ለም አፈር እና ውኃ ተጠቅሞ ምርታማነትን ለማሳደግ ሌት ተቀን ለመሥራት ተነስተናል ነው ያሉት።
በውይይት መድረኮቹም ሕዝቡ የልመና ባሕልን ለማስቀረት ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ጠቅሰው በ100 ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩ የተቀመጠው አንዱ አቅጣጫም ይኸው እንደኾነ አስረድተዋል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባን ገጽታ የሚቀይሩ፣ ለነዋሪዎቿ ኑሮ እና ለመዝናኛ የሚመቹ የኮሪደር ልማቶች በተቀናጀ መልኩ በመተግበር ውጤት መምጣቱን አንስተዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህንን ተሞክሮ ወደ ክልሎች በማስፋት በአብዛኛዎቹ ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በአምራች ኢንዱስትሪ እና በማዕድን ዘርፍ ያለውን ውጤታማነት ለማሳደግ የፋብሪካዎችን አቅም በእጥፍ የማሳደግ ሥራ ትኩረት እንዲሰጠው አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል።
ይህም ከአንድ ዓመት በኋላ ከዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።
በጥቅሉ በዚህ ዓመት የተተነበየውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት የሚያስችል አመላካች ውጤት መኖሩን ጠቅሰው በመጪው በጀት ዓመትም ከ8 ነጥብ 3 በመቶ ያላነሰ ዕድገት እንዲመዘገብ ታቅዷል ብለዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በበጀት ዓመቱ የዝግጅት ምዕራፍ የሚል የጊዜ ሰሌዳን በማስቀረት በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገባ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!