
ደብረ ብርሃን: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሕጻናት ደኅንነታቸው ተጠብቆ የሀገር ተረካቢ እንዲኾኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሕጎች እና ስምምነቶች ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እየተጣሱ ሕጻናት ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈጸሙም ይስተዋላል፡፡
በሀገሪቱ በሚስተዋለው አለመረጋጋት እና የሰላም ችግር ሕጻናት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን በሰላም እጦቱ ምክንያት ከ115 ሺህ በላይ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ መራቃቸውን የዞኑ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ የሮምነሽ ጋሻውጠና ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ችግር ከ11ሺህ በላይ ሕጻናት ያለ ዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽመውባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በተለይ ጉዳት የደረሰባቸውን እና ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን የህክምና፣ የሥነልቦና እገዛን እና የተለያዩ ድጋፎች ስለመደረጋቸው ኀላፊዋ አስታውሰዋል፡፡ ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ማንኛውንም ችግሮች በመከላከል፣ በማስተማር እና መብታቸውን በማክበር ሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባ መምሪያ ኀላፊዋ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ፋንታነሽ መሃመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!