“የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል ነው” ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ

59

እንጅባራ: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪ ናቸው ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ። ውልደታቸው በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ነው። ያኔ መሰረተ ልማት ባልተሟላበትና ትምህርት ቤቶችን በቅርበት ማግኘት በማይቻልበት ዘመን ችግሮችን ተቋቁመው በመማር አሁን ለደረሱበት ከፍተኛ ማዕረግ በቅተዋል፡፡

የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ትምህርት ብቻ እንደኾነ በፅኑ የሚያምኑት ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ አሁን ያለው ትውልድ እሳቸው ያለፉበት እጣ ፋንታ እንዳይገጥመው በማሰብ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ፋግታ ለኮማ፣ አንከሻ ጓጉሳ፣ አየሁ ጓጉሳና ባንጃ ወረዳዎች ረጂ ድርጅቶችንና በጎ ፈቃደኛ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር ትምህርት ቤቶችን አስገንብተዋል፤ ድልድይም አሠርተዋል።

ፕሮፌሰሩ ለትምህርት ቤቶች ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው አድርገዋል። ለዚህ በጎ ሥራቸውም በትውልድ አካባቢያቸው አዘና ከተማ ያስገነቡት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡ በእሳቸው አስተባባሪነት “ፓርትነርስ ኢን ኢዱኬሽን ኢትዮጵያ” በተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅትና በኅብረተሰብ ተሳትፎ ጥምረት በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኘው የዊንዲጊ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ 70 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ በአሁኑ ወቅትም ፓርትነርስ ኢን ኢዱኬሽን ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅትና ሌሎችንም በጎ አድራጊ ግለሰቦችን በማስተባበር በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ የዊንዲጊ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን በማስገንባት ላይ ናቸው። የትምህርት ቤቱ ግንባታ 12 መማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን የያዙ ስምንት ብሎኮች ያሉት መኾኑ ተገልጿል። ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረግበታልም ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

የመማር ማስተማር ሥራን የሚያሳልጡ የቤተ ሙከራ፣ የአይሲቲ ማዕከል፣ የቤተ መጽሐፍት፣ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያና የመፀዳጃ ቤት ክፍሎችም በግንባታው መካተታቸውን ፕሮፌሰር ጌትነት ገልጸዋል። የትምህርት ቤቱ ግንባታ አሁን ላይ 70 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል። ግንባታውን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ዝግጁ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ነው ያነሱት።

“የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል። የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ገበየሁ በሪሁን በፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ አስተባባሪነት በወረዳው እየተገነቡ ያሉ ትምህርት ቤቶች የወረዳውን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ መገንባት ተማሪዎች በአቅራቢያቸው ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል እንደኾነም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ
Next article“ተጨማሪ የጃፓን ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሠራ ነው” በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር