
ሰቆጣ: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአካባቢያችን ያለው ሰላም ክልል አቀፍ ፈተናችንን በአግባቡ እንድንፈተን አግዞናል ሲሉ በሰቆጣ ከተማ ውስጥ የ8ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ተናግረዋል። ከሰኔ 04 እስከ 05/2016ዓ.ም ድረስ የሚሰጠው የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሁሉም ወረዳዎች እየተሰጠ ይገኛል።
ተማሪ ሀና ጌታቸው “ዓመቱን ሙሉ ያለምንም መቆራረጥ የተከታተልነውን ትምህርት በውጤት ለማጀብ ተረጋግተን የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተዘጋጅተን እየተፈተንን ነው” በማለት ገልጻለች። የኩረጃ ባሕልን በመጠየፍ ብቁና ተወዳዳሪ ለመኾን ዓመቱን ሙሉ ተዘጋጅቻለሁ ያለው ደግሞ ተማሪ ዮሐንስ ፈቃዱ ነው። አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚያስገባ ነጥብ ለማምጣት መዘጋጀቱንም ገልጿል። አላማችንን እና እቅዳችንን ለማሣካት በአካባቢያችን ያለው ሰላም ትልቅ ዋጋ አለው ያለችው ደግሞ ተማሪ ገበያ ሞገስ ናት።
የሌትናል ጀኔራል ኃይሉ ከበደ 1ኛና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሰውመሆን ሞላ ሁሉንም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ እንዲያስመዘግቡ እና ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአዳሪ ትምህርት ቤት መግቢያ ነጥብ እንዲያስመዘግቡ አቅደው ሲሠሩ እንደከረሙ ገልጸዋል።
የብሔረሰቡ ትምህርት መምሪያ ኀላፊው ሰይፈ ሞገስ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ 8 ወረዳዎች ውስጥ በ147 ትምህረት ቤቶች 7 ሺህ 993 ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እየወሰዱ እንደኾነ ገልጸዋል። ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ ፈተናውን እንደጀመሩ ሁሉ እስከመጨረሻው ቀን ድረስ ተረጋግተው እንዲፈተኑም አሳስበዋል።
በቀጣይም የሚሰጡ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን በሰላም ለማስፈተን ሰላማችን በዘላቂነት ልናስቀጥል ይገባል ሲሉም አቶ ሰይፈ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:-ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!