
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፈተናው በዘጠኝ ትምህርት ቤቶች ሲማሩ ለቆዩ 1ሺህ 369 ተማሪዎች እየተሰጠ መኾኑን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ አስራት በሪሁን ገልጸዋል። መምሪያው ከወልድያ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተማሪዎችን ውጤት ለማሳደግ ታሳቢ በማድረግ ለተፈታኝ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እና የሥነልቦና ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ነው ያስረዱት።
ኮሌጁ ለከተማ አሥተዳደሩ እና ለሰሜን ወሎ ዞን ተፈታኞች ወጥ የሞዴል ፈተና ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል። አሚኮ የመልካ ቆሌ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል እና የወልድያ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤቶችን የፈተና አሰጣጥ ተመልክቷል።
የመልካቆሌ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አክሊሉ ከበደ እና የወልድያ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሙሉቀን አራጌ ተማሪዎቻቸውን ለማብቃት ዓመቱን ሙሉ መምህራን ሢሠሩ እንደቆዩ እና ተማሪዎች የፈተናውን ባህሪ እንዲለምዱት የሚያደርጉ መልመጃዎችን በጋራ ሢሠሩ መቆየታቸውን ነግረውናል።
የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የከተማ አሥተዳደሩ ተማሪዎች ፈተናውን በስኬት እንዲያጠናቅቁ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የፈተናው ሂደት ሰላማዊ እንዲኾን የድርሻቸውን እየተወጡ ያሉ ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻዎችን አመሥግነዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!