
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰጠ ታደሰ የ2016 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ዙር የ8ኛ ክፍል ፈተና በ358 ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ ነው ብለዋል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች 16 ሺህ 784 ተማሪዎች ለፈተና እንደተቀመጡም ጠቅሰዋል፡፡ አሚኮ በጉባላፍቶ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ስር የሚገኙ የዶሮ ግብር አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የሀራ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የፈተና አሰጣጥ ተመልክቷል።
የጉባላፍቶ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸው የማነ በተሠራው የተቀናጀ ሥራ ፈተናው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው ብለዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ለፈተናው ስኬት ቅድመ ዝግጅት ስለማድረጋቸውም አብራርተዋል፡፡
የዶሮ ግብር አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እሸቱ ጫኔ እና የሀራ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሙሀመድ ይማም ተማሪዎቻቸውን ለውጤት ለማብቃት በትምህርት ዘመኑ ትኩረት ሰጥተው ሲደግፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ተማሪዎቹን በዕውቀትም በሥነልቦናም ስለማዘጋጀታቸው ነው የተናገሩት ፈተናውም በስኬት እንዲጠናቀቅ ከትምህርት ቤቱ የወላጅ እና የቀበሌ አደረጃጀቶች ጋር በጥምረት እየሠሩ መኾኑን ነግረውናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!