ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥበትን ቀን ይፋ አደረገ።

58

አዲስ አበባ: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አሰጣጥን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል። በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና ከ700 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተናውን እንደሚወስዱ የገለጹት የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ካሳ ናቸው፡፡ የፈተና መርሐ ግብሩም:-

👉ለማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ከሐምሌ 03 እስከ ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም
👉ለተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ከትግራይ ክልል ውጪ ከሐምሌ 09 እስከ ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም ፈተናው ይሰጣል ብለዋል።

ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል ሙሉ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የጸጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች ጋር ተያይዞ በተለይም በአማራ ክልል የሚገኙ እና ምዝገባቸውን ያካሄዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በመጀመሪያው ዙር እንደሚፈተኑ ገልጸዋል። ፈተናውን መውሰድ ያልቻሉ ተማሪዎች ደግሞ መስከረም/2017 ዓ.ም በሁለተኛው ዙር ፈተናውን መውሰድ ይችላሉ ብለዋል።

በማኅበራዊ ሳይንስ 369ሺህ 60 በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ 332ሺህ 429 በድምሩ 701ሺህ 489 የ12ኛ ክፍል ፈተና ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል። ፈተናው በበይነመረብ እና በወረቀት እንደሚሰጥም ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ባቀረበችው ሃሳብ ለመደገፍ ተስማማ።
Next article“ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ፈተና እየወሰዱ ነው” የሰሜን ወሎ ዞን