የጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ባቀረበችው ሃሳብ ለመደገፍ ተስማማ።

19

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አሜሪካ በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ያቀረበችውን ባለሦስት ክፍል የሰላም አማራጭ ለመደገፍ ስምምነት ላይ ደረሰ። የተኩስ አቁም አማራጩ ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ በሐማስ የተያዙ የእስራኤል ታጋቾች እንዲለቀቁ እና የፍልስጤም እስረኞች በምትኩ ከእስር ነፃ እንዲወጡ የሚል ነው፡፡

የሰላም አማራጩን ከ15 የጸጥታው ምክር ቤት አባላት 14ቱ ሲደግፉ ሩሲያ ድምጸ ተአቅቦ አድርጋለች። የተኩስ አቁሙን እስራኤል መቀበሏን እና ሐማስም መስማማት እንዳለበት ተገልጿል። የተኩስ አቁም አማራጩን ለመደገፍ የጸጥታው ምክር ቤት መስማማቱ በርካታ ሀገራትን እና የቡድን 7 ሃብታም ሀገራትን ድጋፍም እንዲያገኝ ይረዳዋል ሲል የቢቢሲ ዘገባ ጠቁሟል።

በግንቦት ወር መጨረሻ ፕሬዚዳንት ባይደን ይፋ ያደረጉትን ይህን የተኩሰ አቁም አማራጭ የእስራኤል የሰላም ትልመ ሃሳብ ሲሉ ባይደን ገልጸውታል። ሦስት አባላት ያሉት የእስራኤል የጦር ካቢኔ በሃሳቡ ቢስማሙም የተወሰኑ ሚኒስትሮች ከወዲሁ እንደማይቀበሉት አቋማቸውን አሳውቀዋል። በጉዳዩ ላይ ኔታኒያሁም አቋማቸውን በግልጽ አላሳወቁም።

የተኩስ አቁም አማራጩን ለመደገፍ በጸጥታው ምክር ቤት ስምምነት ላይ ከመደረሱ ቀደም ብሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የቀጣናው ሀገራት መሪዎችን አግኝተው አነጋግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በንግግራቸውም ተኩስ እንዲቆም የምትፈልጉ ከኾነ ሐማስ እንዲስማማ ጥረት አድርጉ በማለት ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበድርቅ ተጎድተው የከረሙ አካባቢዎች አምርተው ራሳቸውን እንዲችሉ እየተሠራ ነው።
Next articleትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥበትን ቀን ይፋ አደረገ።