
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በድርቅ እና በጸረ ሰብል ተባይ ሰብላቸው ለተጎዳባቸው አካባቢዎች ዘር ለማቅረብ እየተሥራ መኾኑን ግብርና ቢሮ ገልጿል። በአማራ ክልል በ2015/16 የምርት ዘመን በ8 ዞኖች በሚገኙ 46 ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ እና የአንበጣ ወረራ ምክንያት በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግር ተጋልጠዋል።
በምርት ዘመኑ በድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች ደግሞ ሰሜን ጎንደር ዞን አንዱ ነው። በዞኑ ጃናሞራ ወረዳ አኹጫራ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ተሻገር ድምጹ እንደነገሩን በምርት ዘመኑ ባጋጠመው ድርቅ ከ1 ሺህ 200 በላይ የአካባቢው አባወራዎች ለችግር ተጋልጠዋል። በ2016/17 የምርት ዘመን በባለፈው ዓመት የታጣውን ምርት ለማካካስ አርሶ አደሮች ማሳቸውን የማለስለስ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ነግረውናል።
አርሶ አደር ተሻገርም አንድ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን የማሳ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። ለአንድ ሄክታር መሬት ደግሞ አንድ ኩንታል ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ እስከ አሁን በቀበሌው የቀረበውን ከ40 ኩንታል የማይበልጥ የስንዴ ዘር ለአካባቢው አርሶ አደሮች ለማዳረስ አስቸጋሪ እንደኾነ አንስተዋል። ቀድሞ የሚዘራ በቂ ዘር በወቅቱ እንዲቀርብም ጠይቀዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ እንዳሉት በ2015/16 የምርት ዘመን በ6 ወረዳዎች በሚገኙ 83 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል በድርቅ ተጎድተዋል። በዚህም 76 ሺህ 277 ሄክታር መሬት ላይ ሊገኝ የነበረ 878 ሺህ 623 ኩንታል ምርት ከጥቅም ውጭ ኾኗል። 414 ሺህ 577 ሰዎችም በድርቁ ተጎጅ ኾነዋል።
ባለፈው የምርት ዘመን የታጣውን ምርት ለማካካስ ጠንካራ የዘር አቅርቦት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ኀላፊው ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ለመኸር ምርት ለማቅረብ ከታቀደው 11 ሺህ 876 ኩንታል ዘር እስከ አሁን ማቅረብ የተቻለው 2ሺህ 541 ኩንታል ብቻ ነው። የምርጥ ዘር የዋጋ መጨመር እና የጸጥታ ችግር ደግሞ በምክንያትነት ተቀምጠዋል። አሁን ላይም ዘር ለማቅረብ በግዥ በሂደት ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
በ2015/16 የምርት ዘመን የታጣውን ምርት ለማካካስ እና አርሶ አደሮችን ከተረጅነት ለማላቀቅ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ዘር እና ሌሎች ግብዓቶችን በወቅቱ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንዳሉት ደግሞ በ2015/16 የምርት ዘመን በድርቅ እና በጸረ ሰብል ተባይ በተጠቁ አካባቢዎች በተለያዩ ድርጅቶች እና በመንግሥት በኩል የዘር አቅርቦት ሥራ ተሠርቷል።
አሁን ላይም ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በ71 ሚሊዮን ብር 8ሺህ ኩንታል የሚኾን የሩዝ እና የስንዴ ዘር ግዥ እየተፈጸመ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 600 ኩንታል የሚኾነው ዘር ለሰሜን ጎንደር የሚሰራጭ ይኾናል። እስከ ሰኔ 10/2016 ዓ.ም ድረስ ወደ ወረዳዎች ተደራሽ ይኾናል ነው የተባለው።
ከዚህም ባለፈ ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል በግብርና እና ጤና ሚኒስቴሮች እንዲሁም በክልሉ በተለቀቀ ገንዘብ በሥርዓተ ምግብ መርሐ ግብር የታቀፉ ወረዳዎች እንደ በቆሎ፣ ቦሎቄ አኩሪ አተር፣ ሽንብራ የመሳሰለ የሰብል ዘር እንዲገዙ መደረጉን ገልጸዋል። ባለፈው የምርት ዘመን በድርቅ እና ተባይ ሰብላቸው ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች በ2016/17 የምርት ዘመን እንዲያካክሱ ተቋማት፣ ድርጅቶችም ኾኑ ግለሰቦች ዘር እና ማንኛውንም የግብርና ግብዓት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!