
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ዘጠኝ ወራት 109 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 232 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ። ላለፉት ወራት በግጭት ውስጥ የቆየው የአማራ ክልል በርካታ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳቶችን አስተናግዷል።
ምንም እንኳን ክልሉ ባላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ለወራት ቢቆይም ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን በርካታ የልማት ሥራዎች ተሰርቷል ተብሏል። ከሰሞኑም የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸው ይታወሳል። ዛሬ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከሃይማኖት አባቶች ጋር በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ዙሪያ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ እና ሌሎች የክልል እና የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባዩህ አቡሃይ በችግር ውሰጥም ኾኖ በርካታ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውሰጥ 109 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 232 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰዳቸውን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ኮምዩኒኬሽን መምሪያ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንዳገኘነው መረጃ በከተማዋ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የከንቲባ ችሎት አገልግሎት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከገባንበት ግጭት እና ጦርነት በመውጣት የጎንደር ከተማን የመልማት እድሎች መጠቀም እንዲቻል ሁላችንም ለሰላም ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!