“የሃይማኖት አባቶች ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል” አቶ ደሳለኝ ጣሳው

67

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከሃይማኖት አባቶች ጋር በሰላም ግንባታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ ደሳለኝ ጣሳው እንደገለጹት የሃይማኖት አባቶች ለሰላም ግንባታ ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።

አሁን ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም መስፈን የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበረም አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች ከማንኛውም ዘመን ወለድ የፖለቲካ ሴራ ነጻ ኾነው ለሰላም ሊሰብኩ ይገባል ብለዋል አቶ ደሰለኝ። የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው የአማራ ክልል ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም በመኾኑ የሃይማኖት አባቶች ለሰላም ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

እርስ በእርስ ከመጠፋፋት በመውጣት ሰላማዊ ሕይዎት ለመኖር ሁላችንም ለሰላም መሥራት ይገባናል ብለዋል። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ የአማራን ሕዝብ ለመታደግ ከአጉል ፍክክር እና እልህ በመውጣት ወደ ቀልባችንን ተመልሰን ለሰላም ልንሠራ ይገባል ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም ግንባታ ከፍተኛ ሚና ያላቸው መኾኑን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሃይማኖት አባቶች ከልብ መሥራት ከቻሉ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚችሉ ገልጸዋል። አሁን ያለው የጸጥታ ችግር በምጣኔ ሃብታዊ እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ስለኾነ በፍጥነት ማረም ያስፈልጋል ብለዋል። ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር በመንግሥት እና በሕዝብ በኩል መተማመን መፍጠር አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ !
Next article109 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 232 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።