
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 76 ነጥብ 64 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሐሙሲት – እስቴ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በመልካም የአፈጻጸም ደረጃ ይገኛል። በመንገድ ግንባታው እስካሁን የጠረጋ ፣ የውኃ መፋሰሻ ፣ የአፈር ፣ የሰብ ቤዝ፣ ቤዝ ኮርስ ፣ የአስፋልት ንጣፍ እንዲሁም የስትራክቸር ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡የግንባታው አጠቃላይ አፈጻጸምም በአሁን ወቅት 51.66 በመቶ ደርሷል፡፡
በተጨማሪም የአነስተኛ እና ከፍተኛ ከልቨርቶች እንዲሁም የሰባት ድልድዮች ግንባታ ሥራም በፕሮጀክቱ ተካትቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ዓለም አቀፉ ኒንዢያ ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ግንባታውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ኻቲብ እና አለሚ ኮንሰልቲንግ ከ ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ጋር በጣምራ የግንባታውን ጥራት የመቆጣጠር እና የማማከሩን ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚኾነው ከ1 ቢሊዮን 394 ሚሊዮን በላይ ብር ወጪ የተሸፈነው በአረብ ባንክ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት (BADEA) ፣በኦፔክ ፈንድ ለዓለም አቀፍ ልማት (OFID) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ የሐሙሲት – እስቴ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ በከተማ ከ21 እስከ 22 ነጥብ 5 ሜትር እንዲሁም በገጠር ከ 8 እስከ 10 ሜትር የመንገዱን ትከሻ ጨምሮ አጠቃላይ የጎን ስፋት የሚኖረው ይሆናል፡፡
በአካባቢው የሚስተዋለው የጸጥታ ስጋት፣ በመንገዱ ክልል ውስጥ የሚገኙ ንብረቶች በወቅቱ አለመነሳት እንዲሁም የካሳ ክፍያ መዘግየት በግንባታው ሂደት ውስጥ የገጠሙ ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በኩል ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና የመስተዳድር አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የግብርና ምርቶች አምራች የኾኑትን የእስቴ እና ደራ ወረዳን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የሚያስተሳስር በመኾኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥቅሞችን የሚሰጥ ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!