
ደሴ: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን በሰላማዊ መንገድ እየወሰዱ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን አሥታውቋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ዓለምነው አበራ በዞኑ 620 ትምህርት ቤቶች ፈተናውን እያስፈተኑ መኾኑን እና 112 የፈተና ማዕከላት ተዘጋጅተው ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ እና ተቋማት ለተማሪዎች ምግብ በማዘጋጀት የፈተናውን ሂደት እያገዙ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው አንስተዋል፡፡ ለአብነትም በአልቡኮ 3 ቀበሌዎች ከ140 ሺህ ብር በላይ በማሠባሠብ ተማሪዎችን በመመገብ ላይ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በኩታበር ወረዳ በመገኘት የፈተናውን ሂደት ተመልክተዋል፡፡ ፈተናው ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናዎናቸውንም አንስተዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው በቀጣይ የ6ኛ እና የ12 ክፍል ፈተናን በስኬት ለማስፈተን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከ8ኛ ከፍል የፈተና ሂደት ተሞክሮ በመውሰድ ሁለቱንም የፈተና እርከኖች በሰላማዊ ሁኔታ ለመፈጸም እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!