
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ስብሰባው የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል። ረቂቅ አዋጁን ላለፉት ሦስት ወራት በዝርዝር ሲመለከቱ የነበሩት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት እና ስፖርት ጉዳዮች እና የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ገጹ እንዳጋራው የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ አዋጁ ላይ የተካተቱ ዋና ዋና ሃሳቦችን በዝርዝር አቅርበዋል። የሕዝብ በዓላት ለዜጎች ሥነ-ምግባር እና ሥነ-ልቦና ግንባታ እንዲሁም ለሀገር እና ለሕዝብ ያላቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ስለመኾኑ በውሳኔ ላይ ሃሳቡ ተብራርቷል።
የሕዝብ በዓላት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴታቸውን ጠብቀው በሰላም በድምቀት እና የዜጎችን የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነት እና መተሳሰብ በሚያጎለብት ሁኔታ እንዲከበሩ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። የሕዝብ በዓላት አከባበር እና ሥርዓት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መኾኑ እና ለሀገራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያላቸው በመኾኑ ከመንግሥት የሚጠበቀውን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ እንዲሁም በቂ የሚዲያ ሽፋን የሚሰጥ እንደኾነም በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተብራርቷል።
የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ ባቀረቡት ሃሳብ እና ጥያቄ አንዳንድ የሃይማኖት ተቋማት በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት እንዳላደረጉ እና ቅሬታ እንዳላቸው ጠቁመዋል። በምክር ቤቱ የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የተወከሉ የሃይማኖት አባቶች በረቂቅ አዋጁ ላይ ስለመወያየታቸው አስረድተዋል።
ነባሩ የሕዝብ በዓላት እና የዕረፍት ቀን መወሰኛ አዋጅ የሕዝብ በዓላት ሲከበሩ ጥቅም ሊያስገኙ በሚችሉ መልኩ በድምቀት የሚከበሩበትን ዝርዝር የአከባበር ሥነ-ሥርዓት አለማስቀመጡም ተመላክቷል፡፡ አዋጁ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር የሚመለከት ሲኾን፣ ክልሎች በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ሕግ አውጥተው በክልል ደረጃ የሚከበሩ አዋጆችን አከባበር መወሰን እንደሚችሉም የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወርቀሰሙ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሕዝብ በዓላት እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አዋጅ ቁጥር 1334/2016 አድርጎ አጽድቆታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!