
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 31ኛ መደበኛ ሥብሠባው የፌዴራል መንግሥት ግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል፡፡ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሳለኝ ወዳጆ ሪፖርት እና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
አዋጁ ከዚህ ቀደም በመንግሥት የግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ሂደት እና ትግበራ ወቅት በአፈፃፀም ሲያጋጥሙ የነበሩ እና ለመልካም አሥተዳደር ችግር ምክንያት ሊኾኑ የሚችሉ የአሠራር ጉድለቶችን ለማረም ወሳኝ እንደኾነ ተገልጿል፡፡ አዋጁ የመንግሥት የግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ከቴክኖሎጂ ለውጥ ጋር መራመድ እንዲችል ለማድረግ እና የሀገር ውስጥ ተወዳዳሪዎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማበረታታት የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን ያካተተ ስለመኾኑም ተጠቁሟል፡፡
ወጥ የኾነ ሀገራዊ የመንግሥት ግዥ እና የንብረት አሥተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አዋጅ እንደኾነም በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተብራርቷል፡፡ አዋጁ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይም ተፈፃሚ እንደሚኾን ተጠቁሟል፡፡ በግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ሂደት የሚከሰት የሕግ ጥሰት የሚያስከትለውን አሥተዳደራዊ ተጠያቂነት ግልጽ የሚያደርግ አዋጅ እንደኾነም ተገልጿል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በአዋጁ አተገባበር ላይ ሃሳብ እና አስተያየት ያቀረቡ ሲኾን፤ አዋጁ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ ሲኾን ተወዳዳሪነታቸውን ሊገድብ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት አንስተዋል፡፡ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሳለኝ ወዳጆ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የመንግሥት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሀገራዊ የግዥ ሥርዓት ሊኖራቸው እንደሚገባ በዓለም አቀፍ ጥናት የተደገፈ ውሳኔ መኾኑን አስረድተዋል።
ይሁን እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተወዳዳሪነታቸውን እና ትርፋማነታቸውን በማይነካ መልኩ የግዥ መመሪያ አዘጋጅተው መሥራት እንደሚችሉ ነው የቋሚ ኮሚቴው ሠብሣቢ ያብራሩት፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው አዋጁ የፌዴራል መንግሥት ግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1333/2016 ኾኖ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!