
ደሴ: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ4 ሺህ 100 በላይ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ፈተና እየወሰዱ መኾናቸውን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ እንዲሰጥ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ ከ4 ሺህ 100 በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች በ37 የመፈተኛ ጣቢያዎች ፈተናው እየተሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የፈተናውን ደኅንነት ለመጠበቅ የጸጥታ አካላት እና የትምህርት ቤት አደረጃጀቶች በመፈተኛ ጣቢያዎች ተገኝተው መታዘባቸውን አስረድተዋል፡፡
ኀላፊው የፈተና ወረቀቶች እና የሌሎች ግብዓቶች እጥረት እንዳይከሰት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመሠራታቸው በሰላማዊ መንገድ ፈተናው እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!