
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የቢሮው የሥራ ኀላፊዎች እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊዎች በባሕር ዳር አካዳሚ እና በአጼ ሰርጸ ድንግል ትምህርት ቤቶች ተገኝተው የፈተና ሂደቱን ተመልክተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኀይለማርያም እሸቴ እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ ማስፈተን ከነበረባቸው 61 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ47 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 6 ሺህ 182 ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ ነው። በባሕር ዳር ዙሪያ የሚገኙ 14 ትምህርት ቤቶች በነበረው የሰላም ችግር በቀጣይ ትምህርት ቢሮ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት ፈተናውን እንደሚወሰዱ ነው የገለጹት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንዳሉት ተማሪዎች የፈተና ሥርዓቱ በሚያዘው መሠረት ፈተናውን እየወሰዱ ይገኛሉ። ለዐይነ ስውራን ተማሪዎችም አንባቢ ተመድቦላቸው እንዲፈተኑ መደረጉን ነው የገለጹት።
በራያ አላማጣ አካባቢ ሕወሓት ፈተናውን የመረበሽ ሙከራ ማድረጉን ያነሱት ኀላፊዋ ክልሉ እና የትምህርት መዋቅሩ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ጥረት ፈተናው እየተሰጠ መኾኑን ነው የተናገሩት። ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሓት እያደረገ ያለውን ትንኮሳ እንዲረዳም ጠይቀዋል።
በ2016 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል184 ሺህ 393 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በመፈተን ላይ ይገኛሉ። ፈተናው ከሰኔ 4/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 5/2016 ዓ.ም ይሰጣል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!