
ሁመራ: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የ8ኛ ክፍል ፈተና ዛሬ መሰጠት እንደተጀመረ ዞኑ አስታውቋል። በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ትምህርታቸውን በአግባቡ ሲከታተሉ የነበሩ 5 ሺህ 197 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ ነው የተባለው።
በዞኑ 108 ትምህርት ቤቶች ላይ ፈተናው እየተሰጠ እንደሚገኝም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረማርያም መንግሥቴ ገልጸዋል። በ2015 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ከ70 በመቶ በላይ ወደ ቀጣይ ክፍል ማለፋቸውን ያስታወሱት የመምሪያ ኀላፊው በ2016 የትምህርት ዘመን በአዲስ መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሰጠ በሚገኘው የ8ኛ ክፍል ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መሠራቱን ተናግረዋል።
ተማሪዎች በፈተናው ውጤታማ እንዲኾኑ ከፈተና በፊት የማካካሻ ትምህርት እና አጋዥ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት ለተማሪዎች በመስጠት ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱንም አንስተዋል። ለተማሪዎች እየተሰጠ የሚገኘው ፈተና በዞኑ በሚገኙ ከተማ አሥተዳደሮች እና ወረዳዎች ያለምንም የጸጥታ ችግር እየተከናወነ ነው።
የፈተና አሰጣጡ ከኩረጃ የጸዳ እንዲኾን “በአንድ ወንበር አንድ ተማሪ” በማስቀመጥ ፈተናው እየተሰጠ እንደሚገኝ እና የፈተና አሰጣጡ ሂደት ጥንቃቄ የተሞላበት መኾኑን በመፈተኛ ትምህርት ቤቶች በመገኘት ማረጋገጣቸውን አቶ ገብረማርያም መንግሥቴ ተናግረዋል። የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን በመጎብኘት ላይ እንዳሉ አሚኮ ያገኛቸው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ገብረዩሐንስ የሽነህ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ ትምህርታቸውን በመከታተል በፈተናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ፈተና እየወሰዱ መኾኑን አንስተዋል።
ሰላም የአንድ ማኅበረሰብ ህልውና ነው ያሉት ኀላፊው ተማሪዎች ያለምንም የጸጥታ ችግር ፈተናቸውን እንዲያጠናቅቁ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!