
ሰቆጣ: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ8ኛ ክፍል ፈተና በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሁሉም ወረዳዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ገልጿል፡፡ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰይፈ ሞገስ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ147 ትምህርት ቤቶች 7 ሺህ 973 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች እየተፈተኑ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት፡፡
ኀላፊው ከባለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት ሢሠራ ስለመቆየቱም ጠቁመዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የ8ኛ ክፍል የማለፍ መጠኑ 75 በመቶ ነበር ያሉት ኀላፊው በዘንድሮው ዓመት 95 በመቶ በላይ ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ እንዲያስመዘግቡ ታቅዶ ሢሠራ ስለመቆየቱም ነው ያብራሩት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያለው አንጻራዊ ሰላም በሁሉም ወረዳዎች ተማሪዎች ለፈተና እንዲቀመጡ ስለማስቻሉ ነው የገለጹት፡፡ አቶ ሰይፈ ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ የተማሩትን ትምህርት በእርጋታ እና በብቃት እንዲፈተኑም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!