
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት የበልግ ተጠቃሚ በኾኑት አካባቢዎች ዘግይተው ለተዘሩ እና ፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች እና ለቋሚ ተክሎች ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
ለጓሮ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች የውኃ ፍላጎትን ከማሟላት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ነው የተገለጸው፡፡
አስቀድመው ለሚዘሩ የመኸር ሰብሎች በወቅቱ ለመዝራት እና ማሳ ለማዘጋጀት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡ በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚጠበቀው የእርጥበት ሁኔታ ረጅም ጊዜ የሚጠይቁ ሰብሎችን ለመዝራት፣ ለቋሚ ተክሎች፣ በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለተተከሉ እና ለሚተከሉ የዛፍ ችግኞች እድገት የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ነው የተባለው።
በሌላ በኩል በሚቀጥሉት ቀናት በዓባይ፣ በላይኛው እና በመካከለኛው ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አዋሽ እና ተከዜ እንዲሁም በጥቂት የአፋር ደናክል ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የእርጥበት ሁኔታን ያገኛሉ ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እንዳለው የእርጥበት ሁኔታው በተፋሰሶች ላይ የሚኖረውን የገፀ ምድርም ኾነ የከርሰ ምድር የውኃ ሃብትን ያሻሽላል፤ ለመስኖም ኾነ ለኃይል ማመንጫነት የሚያገለግሉ የግድቦችን የውኃ መጠን ያሻሽላል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!