
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች፣ የክልሉ መሪዎች እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድፖስት በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ከሕዝቡ ጋር ሰላምን ለማምጣት ያለሙ ውይይቶችን አድርገዋል።
ከመድረኩ በተጓዳኝ መሪዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን በግጭት ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማነቃቃት ያለመ ጉብኝትም አካሂደዋል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ ከሕዝባዊ ውይይት በተጓዳኝ ጥላቻ እና ጽንፈኝነትን በመንቀል ፍቅር እና አንድነትን እንትከል በሚል መሪ መልዕክት የችግኝ ተከላ ተከናውኗል። በወረዳው የተከናወኑ የመስኖ ልማት ተግባራትም ተጎብኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ጥልን በማስወገድ ሰላም እና ፍቅርን ለማጎልበት ያለመ ነው ብለዋል። ዶክተር ድረስ የክልሉ ሕዝብ በመጪው ክረምት የመኸር እርሻ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚከናወንበት ጊዜ በመኾኑ ቀልብን በመሠብሠብ ወደ ልማት ሥራ መመለስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
የአዋበል ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋልተንጉስ ማሞ በአካባቢው የተከሰተው የፀጥታ ችግር በግብርና ሥራው ላይ ጫና ቢፈጥርም በወረዳው ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚውል ከ16 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በተያዘው ክረምት 2 ሺህ 800 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ ሀገር በቀል እና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!