ኢትዮጵያ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን ለማስፈን ቁርጠኛ መኾኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡

13

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሰኔ 3/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 4/2016 ዓ.ም በሩሲያ ፌዴሬሽን ኒዥኒ ኖቭጎሮድ ውስጥ በሚካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚኒስትሮች ሥብሠባ እየተሳተፉ ነው፡፡
ሚኒስትሩ በሥብሠባው ላይ ኢትዮጵያ ለብሪክስ አባልነቷ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ ያላትን የጎላ ሚና ለማሳደግም ከብሔራዊ የልማት ትኩረቶቿ አኳያ የተወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎችን አብራርተዋል። ወቅታዊ እና አንገብጋቢ የኾኑ ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችም በየትኛውም ተቋም ለብቻ ሊፈቱ ስለማይችሉ እውነተኛ ዓለም ዓቀፋዊ አጋርነት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይኾን አስፈላጊ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ልማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዕከል ያደረጉ እና የጋራ መፍትሄዎችን የሚያመላክቱ ውጤታማ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶች በሥብሠባው አጽንኦት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የታዳጊ ሀገራትን ጥቅም ለማስጠበቅም የባለብዙ ወገን ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ የልማት ፋይናንስ እና የእዳ ስረዛን ማሳደግ አስፈላጊ መኾኑን ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ኢትዮጵያ ሰላምን እና እድገትን፣ ሁሉን ዓቀፍ እና ዘላቂ ልማትን እንዲሁም ውጤታማ ባለብዙ ወገን ግንኙነትን በጋራ ለማስፈን ቁርጠኛ መኾኗን አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግጭቱ ቆሞ ሰላም እንዲወርድ የሉማሜ ከተማ እና የአዋበል ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
Next articleከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየወሰዱ መኾናቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።