
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሰላምን ለማምጣት ዓላማ ያደረገ ሕዝባዊ ውይይት ከሉማሜ ከተማ እና ከአዋበል ወረዳ ነዋሪዎች ጋር በሉማሜ ከተማ ተካሂዷል። ወይዘሮ ላቀች ወርቁ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሉማሜ ከተማ በአነስተኛ ኢኮኖሚ ሕይዎትን የሚመሩ እናት ናቸው። ባለፉት 10 ወራት በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ኑሯቸውን ከባድ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ። ግጭቱ ቆሞ ሰላም እንዲወርድም አጥብቀው ይሻሉ።
የሉማሜ ከተማ እና የአዋበል ወረዳ ነዋሪዎችም ሰላምን በማምጣት እንደ ወይዘሮ ላቀች ሁሉ ግጭቱ ኑሯቸውን ያከበደባቸውን ወገኖች ከችግር ለማውጣት ዓላማ ያደረገ ውይይት ክክልሉ መሪዎች ጋር አካሂደዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በጦርነት ችግር አይፈታም፣ እርቀ ሰላም ይውረድ መንግሥት ሕግ እና ሥርዓት ያስከብር ብለዋል። በአካባቢው ሰላም እንዲመጣ የድርሻቸውን ለመወጣትም ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከነዋሪዎች ጋር የመከሩት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች፣ በመሪዎች እና በሙያተኞች የሚነሱ ጉድለቶችን ለማረም ቁርጠኛ ነን ብለዋል። ሕዝቡ ሰላማዊ ሕይዎትን እንዲመራም ልዩነቶችን በንግግር መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ምክንያት የመጣው የዋጋ ንረት ሳያንስ እርስ በእርስ በመገዳደል ሕዝብን ወደ ከፋ ችግር መክተት አይገባም ብለዋል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የፌዴራል እና የክልል ተወካዮች የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች የአዋበል ወረዳ እና የሉማሜ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!