
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን የአዳርቃይ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሚሊዮን ታደሰ እንደገለጹት ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም የሕወሀት ታጣቂ ኃይል በወረዳው አሊ ቀበሌ ድዋር ግቫና በተባለ ቦታ ሰርጎ በመግባት ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል። ጥቃቱን ያደረሰውም ሀጎስ በሚባል ግለሰብ በሚመራ የሕወሀት ኃይል መኾኑን ጠቅሰዋል። በጥቃቱ አብዛኞቹ ሕጻናት የኾኑ 13 ሲቪል እና 2 የጸጥታ አካላት የተገደሉ ሲኾን 500 እንስሳትንም ዘርፎ መውሰዱን ነው ያስረዱት።
ሕወሀት በአካባቢው የጦር ኃይል የማስጠጋት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው የተፈጸመው ጥቃትም የዚያው አካል ነው ብለዋል። ተከዜን ተሻግሮ በመምጣት በዋልድባ ገዳም በኩል በመግባት አርማ ደጋ በሚባለው በረሃ ጥቃቱ መፈጸሙን ነው የገለጹት። አሁን ላይ የወረዳው የጸጥታ ኃይል ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በመተባበር ጥበቃ እያደረገ መኾኑን የገለጹት አቶ ሚሊዮን በየደረጃው ለሚገኝ የመንግሥት አካል ማሳወቃቸውን ነው ያብራሩት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ሕወሀት አርማ ደጋ የተባለውን የአድርቃይ በረሃ እና የስኳር ፋብሪካውን ግድብ አልፎ ሰርጎ በመግባት በንጹሃን ላይ ጥቃቱን ማድረሱን ገልጸዋል። የወረዳው የጸጥታ መዋቅርም በፍጥነት ደርሶ ሕዝቡን ማረጋጋቱን እና ጉዳት ያደረሰው ኃይልም በፍጥነት አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተናግረዋል።
ሕወሓት በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እንደ መነሻ በማድረግ ችግሩን ለማባባስ እና አካባቢውን ለመውረር ያለው ፍላጎት ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ የዞኑ የጸጥታ ኃይል የተጠናከረ ጥበቃ እያደረገ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት። በተለያየ መንገድ እየገቡ በመረበሽ አካባቢውን ያልተረጋጋ ለማድረግ እየሠሩ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት። “እኛም ይህንን ተረድተን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል” ብለዋል።
ሕወለት በፈጸመው ጥቃት ንጹሃን አርሶ አደሮች እና ሕጻናትን ገድሏል፣ እንስሳትን ዘርፏል፣ አካባቢው እንዳይረጋጋ ለማድረግ ሞክሯል ነው ያሉት። ”የሕወሀት ፍላጎት ለማንኛችንም ግልጽ ነው” ያሉት የዞኑ አሥተዳዳሪ ”ሕወሀት የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ በመገምገም አካባቢውን ለማተራመስ እና ዳግም ለመውረር እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” ብለዋል።
በመኾኑም የአማራ ሕዝብ እርስ በእርስ በመግባባት፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት እና አንድነትን በማጠናከር የሕወሀትን የወረራ እንቅስቃሴ ለመመከት አማራ አንድ ኾኖ እንዲቆም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!