
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንዲት እውነት፣ ለማትለወጥ ማንነት እልፍ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ አያሌ መከራዎችን ተቀብለዋል፤ በግፍ ተወግተዋል፤ በግፍ ቆስለዋል፤ በግፍ ታስረዋል፤ በግፍ ተዘርፈዋል፤ በግፍ ተፈናቅለዋል፤ በግፍ ሞተዋል፤ ያለ ቀባሪ በዱር በገድል ተጥለዋል፡፡ በበደለኞች ፍርድ ቤት ሐሰተኛ ፍርድን ተቀብለዋል፤ በሐሰተኞች ችሎት የተዛባች ፍርድን ሰምተዋል፡፡
የራያ እናቶች በግፍ አልቅሰዋል፤ የራያ አረጋውያን ያለ ጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል፤ በደል ሳይገኝባቸው እንደበደለኛ ተቆጥረው፣ ጥፋት ሳይፈጽሙ እንደ ጥፋተኛ ታይተው ከበደልም የከፋችውን፣ ከመከራም የከበደችውን ተቀብለዋል፡፡ ታዲያ መከራው እየበዛባቸው፣ በደሉ እየጸናባቸው፣ ሞቱ እየበረከተባቸው ከእውነታቸው አይወርዱም፤ ከማንነታቸው ዝንፍ አይሉም። ስለጸናች እውነታቸው፣ ስለ ማትለወጥ ማንነታቸው መከራውን እየተቀበሉ እውነትን ይናገራሉ እንጂ፡፡
እውነታቸውን በሐሰት ጉድጓድ ቀብረናታል፤ በሐሰተኛ አንደበት ቀምተን እንዳትናገር አድርገናታል፤ ከመዝገብ ላይ ሰርዘናታል ብለው ነበር፡፡ የራያ እውነት ግን ተቀበረች ከተባለችበት ፈንቅላ ትወጣለች፣ እንዳትናገር ኾናለች ከተባለችበት ከሁሉም ልቃ ትሰማለች፣ ጮሕ ብላ ከዳር ዳር ታስተጋባለች፣ ላልሰሙት ትደርሳለች፣ አንሰማሽም ያሏትን እንቅልፍ ትነሳቸዋለች፤ ከመዝገብ ላይ ተሰርዛለች ስትባል ደምቃ ትነበባለች፣ ጎልታ ትታያለች፣ ትናንትን ዛሬን እና ነገን አስተሳስራ ታሪክን ትዘክራለች፣ እውነትን ትናገራለች፡፡
ራያዎች በግፍ የሚለወጥ ማንነት፣ በውሸት የሚጠፋ እውነት እንደሌለ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ሞት እያጸናቸው፣ መከራ እያበረታቸው ለዓመታት ታግለዋል፡፡ በገዳዮቻቸው ፊት ቆመው እውነትን መስክረዋል፤ በአሳዳጆቻቸው ፊት ቆመው እውነተኛ ማንነታቸውን ገልጠዋል፤ ስለ እውነተኛ ማንነታቸው ሁሉንም ተቀብለዋል፡፡ ራያ ወሎ አማራ ሞት ያላጠፋው እውነት፣ መከራ ያልቀየረው ማንነት ነው፡፡
ሕወሃት ራያን በውሸት እና በአዲስ ማንነት የራሱ ለማድረግ ለዓመታት ጥሯል፡፡ ራሱ ሕግ አውጥቶ፣ ራሱ ድንበር ከልሎ፣ ራሱ ማንነት ሰጥቶ፣ ራሱ አጽድቆ ለዓመታት ግፍ ሲፈጽም ኖሯል፡፡ የራያን አባቶች እነ ዘወልድን፣ እነ መዛርድን፣ እነ ስንዬሰገድን እና እነ ክፍሎን ከፋፍሎ ቆይቷል፡፡ አንደኛው የፈረደውን ሌላኛው የሚቀበለውን፣ አንደኛው ያዘዘውን ሌላኛው የሚፈጽመውን፣ የማይለያዩትን፣ የማይነጣጠሉትን የራያን አባቶች ነጣጥሏቸው፤ ከአንድ አባት እና ከአንድ እናት የሚወለዱ ልጆችን የተለያዬ ማንነት ሰጥቷቸው፣ ድንበር አበጅቶላቸው አለያይቷቸው ነበር፡፡
ዳሩ የእውነት ቀን መምጣቱ አይቀርምና ውሸቱ ሲቋጭበት፣ ዘመኑ ሲያበቃበት፣ የጸናች እውነትን እና ትክክለኛ ማንነትን መቋቋም ሲያቅተው ራያን ለባለቤቶቹ አስረክቦ ነበር፡፡ ራያም ከጥንት ማንነቱ ከአብራኩ ክፋይ ከወሎ አማራ ጋር እንደገና በአንድነት መኖር ከመጀመረ ጊዜያት ተቆጥረው ነበር፡፡
ዳሩ ሕወሃት የማይድን በሽታ አለበትና ለዳግም ወረራ ወደ ራያ መጥቷል፡፡ የራያ አካባቢዎችንም ወርሯል፡፡ ራያም “በመቃብራችን ላይ እንጂ በሕይወት እያለን በሕወሃት አሥተዳደር አንኖርም” ብሏል፡፡ በገዳዮቹ ተከቦ እውነቱን ተናግሯል፡፡ ለከበረች ማንነቱ ራያ አብሯል፡፡ የራያ ነዋሪዎች ስለ ፍትሕ ለማንነታችን ሲሉ በአላማጣ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡ ፍትሕ እንዲሰጣቸው፣ የሕወሃት ወረራ ቡድን እንዲወጣላቸው፣ መከራው እንዲያበቃላቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ተናግረዋል፡፡
የራያ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሞገስ ኃይሉ ሕወሃት ከሥር መሠረቱ አማራን እንደጠላት ፈርጆ የተነሳ፣ በሕዝብ መከራ የሚደሰት ነው ይላሉ፡፡ የራያ ሕዝብ በግፍ የተጫነበትን ማንነት ለማስመለስ ጥያቄውን በሕጋዊ መንገድ አቅርቦ፣ መልሱን በተስፋ እየጠበቀ ኖሯል፤ ሰላማዊ ትግሉ አሁንም ቀጥሏል ነው የሚሉት፡፡ ሰኔ 02/2016 ዓ.ም የተደረገው ሰልፍም እየሞትን፣ እየተንገላታን፣ በራያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ይቁም በማለት ብሶታችን ለማሰማት፣ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን እንዲፈጸም፣ ሕወሃት ትጥቁን እንዲፈታ፣ የማንነት ጥያቄያችን በሕግ አግባብ እንዲፈታለን ለማሳወቅ የተደረገ ነው ይላሉ፡፡
ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ ነው፤ የሕወሃት የግፍ ሥራ በራያ እንደ ጎርፍ እየወረደ ነው፤ ንጹሐን ይገዳለሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ታፍነው ተወስደው ብር እንዲከፍሉ ይደረጋሉ፣ ሰቆቃው ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡
ሕወሃት ቀደም ሲል ሲያደርጋቸው የነበሩ እኩይ ድርጊቶችን አሁን የበለጠ አስፍቶ እየፈጸማቸው ነው፤ እኛ ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟችንን ገልጸናል፤ ፍትሕ እንዲሰጠንም ጠይቀናል፤ እየሞትን፣ እየተሰቃየን ጥያቄያችን በሕጋዊ መንገድ እንዲፈታልን ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን ቀጥለናል ነው ያሉት፡፡
“መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት እንዲተገብር በአክብሮት እንጠይቃለን፣ ሕወሃት በራያ ሕዝብ ላይ የጀመረውን ወረራ ለቅቆ ይውጣ፣ የራያ ሕዝብ ማንነት ጥያቄ በሀገር አፍራሾች አይቀለበስም” የሚሉ እና ሌሎች መልእክቶችን ይዘን ወጥተናል ነው ያሉት።
ሕዝቡ የሕወሃት ታጣቂዎች ባሉበት ከጫፍ እስከ ጫፍ ወጥቶ ሀሳቡን ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ እና ለመንግሥት አድርሷል፡፡ ሕዝቡ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ይሰጠኛል፤ የማንነት ጥያቄዬ በሕግ አግባብ ይመለስልኛል፤ ሰውን በመግደል መፍትሔ አይመጣም፤ ትክክለኛው የመታገያ መንገድ ሰላማዊ ትግል ነው ብሎ ያምናል ይላሉ፡፡
መንግሥት ቃል በገባው መሠረት እየፈጸመልን አይደለም፤ ቃሉን አክብሮ እንዲፈጽምልን ሕዝቡ ግፊት እያደረገ ነው፣ ነገር ግን መንግሥት እንደሚመልስለት ያምናል፤ ራያ ወሎ ነው፣ ወሎም አማራ ነው፤ ራያ የአማራ ክፋይ ነው፣ አሁንም በመንግሥታዊ ሥርዓት ጠንካራ እምነት እና አቋም አለው፤ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታለትም ግፊት ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
የራያ ሕዝብ ጥያቄ የፍትሕ፣ የእውነተኛ ማንነት ነው፤ እያደረገው ያለውም እውነተኛ የፍትሕ ጥያቄዬ በጉልበት እንዳይደፈጠጥብኝ በሚል ነው ብለዋል፡፡ የራያ ሕዝብ የተነሳው አማራ ነህ ተብሎ አይደለም፤ አማራ ስለኾነ አማራ ነኝ ብሎ ነው እንጂ ነው የሚሉት፡፡ ሕጋዊ ጥያቄ ያቀረበው ራሱ ሕዝቡ ነው፤ “አማራ ነኝ” ብሎ የእውነት ጥያቄ ነው ያቀረበው ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ባለው አቅም ሁሉ ራያን ሲረዳ ቆይቷል፤ አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ግን ክልሉ በተገቢው መንገድ እንዲደግፍ አላስቻለውም፤ ሕወሃትም ይሄንን አጋጣሚ ይዞ እንደመጣ እናውቃለን ብለዋል። ክልሉ በችግር ውስጥም ኾኖ ድጋፉንም አጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ወቅታዊ ችግሩ ይዞት እንጂ እንደ ራያ ሕዝብ ሁሉ ጠያቂ ነው ይላሉ፡፡
የራያ ሕዝብ እውነትና ፍትሕን የሚጠይቅ፣ ታላቅና ኩሩ ሕዝብ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የራያ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው በወረራ ውስጥ ኾኖ ነው፣ ምግብ መብላት አልቻለም፤ ወራሪዎች ግፍ እያደረሱበት ነው ብለዋል። የትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር መሪዎች ግማሾቹ ታጣቂዎችን እያስወጣን ነው፤ ግማሾቹ ደግሞ እንይዛለን ይላሉ። መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን የወረራ አድማሳቸውን እያሰፉ ነው ብለዋል፡፡
ስምምነቱ እንዲፈርስ የተለያዩ በሮችን እየከፈቱ ነው፤ አንድም ታጣቂ አላስፈቱም፣ ከመንግሥት እና ከሌሎች ተቋማት የሚያገኙትን ድጋፍ እና ድጎማ ለወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አላማ ነው የሚያውሉት፣ አሁንም ወታደራዊ ሥልጠናዎችን እየሰጡ ነው ነው ያሉት። የራያ እና የወልቃይት ጥያቄ የመላው አማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ነው፤ ሕዝቡ በአንድነት ኾኖ የሕወሃትን ሴራ ማክሸፍ አለበት ነው ያሉት፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን የእውነተኛ ጥያቄያችን እንዲመለስ፣ ፍትሕ እንዲሰጠን አብረውን እንዲቆሙ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
“የትግራይ ሰዎች ከቀልባቸው ሊኾኑ ይገባል፤ ከዚህ በኋላ በጉልበት የሚገዛ ሕዝብ አይኖርም፤ እውነተኛው የሕዝብ ጥያቄ የትኛውን ነው ብላችሁ ሕዝብ ላይ አፈሙዝ ባትስቡ ጥሩ ነው፤ የራያ ሕዝብ ጥያቄ በፍትሕ ይረጋገጣል፤ ነገ ግን ኋላ እንዳንተዛዘብ፣ መልካም ጉርብትናችን እንዳይሻክር ጥንቃቄ ልታደርጉ ይገባል” ብለዋል በመልእክታቸው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!