“የመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ሕዝባዊ አደራቸውን ሊወጡ ይገባል” ደሳለኝ ጣሰው

50

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ያለመ የምክክር መድረክ አካሂደዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አሥተባባሪ እና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው የመንግሥት ሠራተኞች ቀልጣፋና ታማኝነት ያለው አገልግሎት በመስጠት ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር ችግሮች በመፍታት የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የመንግሥት ሠራተኞች ዋነኛ ኃይል መኾናቸውንም ገልጸዋል ። “ሁላችንም ውስጣችንን አይተን በመፈተሽ ለሕዝባችን ፈጣንና ታማኝነት ያለው አገልግሎት በመሰጠት እና ዜጋ ተኮር ተቋም በመገንባት ኅላፊነትን መወጣት ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል። ሀገራችን የሁላችንም በመኾኗ በችግሮቻችን ላይ በመወያየት ችግሮቻችንን የመፍታት ኀላፊነት አለብን ነው ያሉት።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ባለፉት 10 ወራት ከፀጥታ ሥራ ጎን ለጎን በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሕዝቡ በከፋ ችግር ውስጥ ማለፉን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንዱ መነሻ ምክንያት የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የወለደው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኾኑን ገልጸዋል ።

ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሕዝብና መንግሥት መተማመን ያስፈልጋል፤ ለዚህም የመንግሥት ሠራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መፍታት መቻል አለባቸው ብለዋል። ሰላም መስፈኑን ተከትሎ መሪዎች እና ባለሙያዎች በቁርጠኝነት በመሥራታቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ከምንጊዜውም በላይ መፈጸም መቻሉን ገልጸዋል።

ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በቀጣይም ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው የሕዝብን ችግር እንዲፈቱ ሰላምን በማስጠበቅ ሥራን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰላም እና በአብሮነት የመኖር ባሕልን ለማስቀጠል ሕዝቡ በጋራ መሥራት እንዳለበት ተገለጸ።
Next articleየሉማሜ ከተማ እና የአዋበል ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሰላም ጉዳይ ላይ እየመከሩ ነው፡፡