በሰላም እና በአብሮነት የመኖር ባሕልን ለማስቀጠል ሕዝቡ በጋራ መሥራት እንዳለበት ተገለጸ።

22

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም እና በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኘው ኮር በአዊ ዞን ከዚገም እና አጎራባች ወረዳዎች ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ወንድማማችነትን የሚያጠናክር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡ የምክክር መድረኩን የመሩት የኮማንድ ፖስቱ ሠብሳቢ እና የኮሩ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ሕዝቡ ተከባብሮ እና ተቻችሎ የመኖርን ጥበብ የተካነ ደግ አሥተዋይ እና አቃፊ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡

ጽንፍ የወጡ ቡድኖች የጥፋት አጀንዳቸውን ለማስፈጸም በዘር እና በሃይማኖት እየከፋፈሉ በፈጠሩት ግጭት ብዙ ሕይወት ጠፍቷል ሀብት ወድሟል፣ ሕዝብ ተፈናቅሏል ብለዋል። አዛዡ የጥፋት ኀይሉ አላማ ቢስ የግል ጥቅሙን ለማሳካት የተደራጀ መኾኑን በውል ተገንዝቦ በሰላም እና በአብሮነት የመኖር ባሕሉን ለማስቀጠል ሕዝቡ በጋራ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎችም ከጥንት ጀምሮ ተከባብረን፣ ተቻችለን፣ ተጋብተን እና ተዋልደን በደም ተሳስረን የኖርን በመኾኑ ሕዝቡን ለመለያየት የሚሠሩ ቡድኖች ካሉ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ እንሠራለን ብለዋል፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በእለቱም የሕዝቡን አብሮነት በጋራ የመኖር ባሕሉን የሚያሳዩ ኪነታዊ ትዕይንቶች ቀርበዋል። በማንኛውም ጊዜ ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጋር አብሮ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አሚኮን ጨምሮ ከስድስት የመገናኛ ብዙኅን ተቋማት ጋር የአየር ሰዓት ግዥ ውል ተፈራረመ።
Next article“የመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ሕዝባዊ አደራቸውን ሊወጡ ይገባል” ደሳለኝ ጣሰው