የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን መተግበር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተጠናቅቆ ለውይይት ዝግጁ መኾኑ ተገለጸ።

23

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና ዕርቅ ማውረድ፣ በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምሕረት፣ በተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም በማካካሻ ስልቶች ላይ የተዋቀረ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን የፍትሕ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውሷል።

በፖሊሲው መሰረት ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማት ተቋቁመው ሁሉንም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማስተግበሪያ ስልቶች ሥራ ላይ እስኪያውሉ ድረስ የትግበራ ምዕራፉን የመጀመሪያ ዙር ሥራ የማስተባበር ሚናውን ለመወጣት የትግበራ ሂደቱን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ሲያዘጋጅ መቆየቱን ገልጿል። በዚህም መሰረት በፖሊሲው የትግበራ ምዕራፍ የሚከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር የያዘ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተጠናቅቆ ለውይይት ዝግጁ መኾኑን ይፋ አድርጓል።

በፍኖተ-ካርታው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአባልነት የሚሳተፉበት ጊዜያዊ እና ዘላቂ ተቋማዊ የቅንጅት አመራር ሥርዓት ስለሚቋቋምበት ሁኔታ፤ ስለ ሽግግር ፍትሕ ስልቶች አተገባበር ቅደም-ተከተል መካተቱን አንስቷል። ተመጋጋቢነት እና ተደጋጋፊነት፤ ተቋማቱን ለማቋቋም እና ከተቋቋሙም በኋላ ሥራቸውን ስለሚሠሩበት ሁኔታ የሚደነግጉ የሕግ ማዕቀፎች ስለሚዘጋጁበት ሁኔታ እና የተቋማቱን አቅም ለመገንባት ስለሚሠሩ ሥራዎች የሚያትቱ ዝርዝር ተግባራት ተቀርጸው ተቀምጠዋል ተብሏል፡፡

ፍኖተ ካርታው በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት የክልሎችን፣ የባህላዊ ፍትህ ሥርዓቶችን፣ የተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሚና፣ ተሳትፎ እና ኃላፊነት፣ እንዲሁም የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎችን በተመለከተ የሚተገበሩ ተጨማሪ እርምጃዎችን በውስጡ እንዲይዝ መደረጉም ተብራርቷል።

በሌላ በኩል የሽግግር ፍትሕ በሀገር ወይም በመንግሥት መሪነት እና ሕዝባዊ ባለቤትነት መርህ የሚመራ ሥርዓት እንደመኾኑ መጠን ፖሊሲውን ሕዝባዊ ገጸታ ለማላበስ የፖሊሲውን አስፈላጊነት፣ ይዘት እና የትግበራ ሂደት በተመለከተ ሕዝቡ ያለውን እውቀት ለማሳደግ ስለሚሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ዝርዝር ተግባራት በፍኖተ ካርታው እንዲመላከቱ ተደርጓል፡፡

ከትግበራ ምዕራፍ ረቂቅ ፍኖተ ካርታው በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ጊዜያዊ የተቋማት የቅንጅት አመራር ሥርዓት ማቋቋሚያ ረቂቅ መመሪያ፣ የሽግግር ፍትሕ ስልቶች አተገባበር ቅደም-ተከተል ማብራሪያ ሰነድ መዘጋጀታቸውን ገልጿል። የአጋር ተቋማት ግንኙነት እና ትብብር ማንዋል እና የሽግግር ፍትሕ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነዶች የተዘጋጁ ሲኾን ፖሊሲውን ወደ ተለያዩ ሀገር በቀል ቋንቋዎች የመተርጎም ሥራ መጀመሩንም ጠቁሟል።

የእንግሊዝኛውን ቅጂ የማዘጋጀት ሥራው ከእርማት በስተቀር በአብዛኛው መጠናቀቁንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አንስቷል፡፡ በዚህም መሰረት የፍኖተ ካርታውን ረቂቅ ሰነድ ጨምሮ በተዘጋጁት የማስተግበሪያ ሰነዶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ሲጠናቀቁ የፖሊሲው ትግበራ ምዕራፍ ዋና ዋና ተግባራት መከናወን እንደሚጀምሩ አረጋግጧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበእቅዱ ልክ ጥቅም ያልሰጠው የላሊበላ ማር ሙዚየም
Next articleየኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አሚኮን ጨምሮ ከስድስት የመገናኛ ብዙኅን ተቋማት ጋር የአየር ሰዓት ግዥ ውል ተፈራረመ።