በእቅዱ ልክ ጥቅም ያልሰጠው የላሊበላ ማር ሙዚየም

28

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእንስሳት፣ በማዕድን እና በዕጽዋት ሃብታም እንደኾነ የሚነገርለት የተከዜ ተፋሰስ ምድር አብላጫው ስፋቱ በአማራ ክልል ውስጥ ይገኛል። የፍየል፣ የማር እና የእጣን እምቅ ሃብቶቹም ተጠቃሽ ናቸው። ላስታ – ላሊበላ በተከዜ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ ለማር ምርት ሰፊ አቅም ያለው መልክዓ ምድር በመኾኑም የላሊበላ ማር ሙዚየም ተቋቁሞበታል።

ሙዚየሙ በ2000 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት፣ በ2008 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቅቆ በ2011 ዓ.ም ሥራ የጀመረ ተቋም ነው። ከ5 ሺህ ዓመት በላይ የንብ ማነብ ታሪክ እንዳላት ለሚነገርላት ኢትዮጵያ ላስታ – ላሊበላ በአብነት ከሚነሱ አካባቢዎችም ውስጥ ነው። ከንብ እና ከማር ምርት ጋር በተያያዘም ስሙ ቀድሞ ይነሳል። የአካባቢውን ስም ጠቅሶ ከማድነቅ ባለፈ በተፈጥሮ የታደለውን ሃብት በአግባቡ ተጠቅሞ ሕዝቡን ተጠቃሚ የማድረግ ጉዞው ግን አሁንም ዘገምተኛ ነው።

ይህን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ሃብት በመጠቀም ለንብ እርባታ እና ለማር ምርት ያገለገሉ ቁሶች በሙዚየም በማስቀመጥ ታሪኩን መዘከር፣ የአካባቢውን ዘላቂነት ያለው መስህብ (ኢኮ – ቱሪዝም) ግምት ውስጥ በማስገባት እና በማስጎብኘት ገቢ ለማግኘት፣ ተከዜ ተፋሰስ ለማር ምርት ያለውን ምቹ ተፈጥሮ በመጠቀም ማርን ለማምረት፣ በዘርፉ ጥናት እና ምርምር በማድረግ ምርቱን ለማሳደግ እና አናቢዎችን ለማሠልጠን ታስቦ ተመስርቷል።

ለማር ምርት በተፈጥሮ የታደለው ላስታ – ላሊበላ እና አካባቢው ቅዱስ ላሊበላ ከንብ ጋር ያለው ሃይማኖታዊ ተረክ እንዲሁም 83 ሺ 294 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የተከዜ ተፋሰስ ለንብ እርባታ ተስማሚነት ብሔራዊ ሙዚየሙ በላሊበላ እንዲገነባ ምክንያቶች መኾናቸውን በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብ እና ሐር ልማት ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን ገልጸዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ቀበሌ 06 ነዋሪ አቶ ወንድሙ ማሞ ንብ ማነብ እና ማር ማምረት ላይ ልምዳቸው ከፍ ያለ ነው። የእሳቸው ማር በፍለጋ አይገኝም ይባልለታል። እርሳቸውን መሰል በርካታ አናቢዎችም በተከዜ ተፋሰስ ሞልተዋል። የላስታ ማር፣ የአይና ማር፣ የሰቆጣ ማር እየተባለ ተመርጦ በየሀገሩ ነጭ እና ጥራት ያለው ማር ይሰራጫል። ስለኾነም ላስታ እና ዙሪያው ‘የማር ሀገር ነው’ ተብሎ ላሊበላ የማር ሙዚየም ግንባታ ሲጀመር ተስፋ እንደጣሉበት አቶ ወንድምነው ተናግረዋል። ግንባታው ሲጀመር ”የምታመርቱትን ማር እንረከባችኋለን፤ ሌላም ጥቅም ታገኛላችሁ ተብለናል” ይላሉ።
”እኛ ተሰናድተን ስንጠብቅ ወሬ ኾኖ ቀረ” ያሉት አቶ ወንድምነው የላስታ ማር ሙዚየም በተነገረው ልክ ጠቀሜታ አለመስጠቱን እና ከኮሮና መከሰት ጀምሮ በየጊዜው የሚፈጠረው አለመረጋጋትም ስለ ማር ሙዚየሙ ለመጠየቅ እንዳላስቻላቸውም ገልጸዋል።

በሙዚየሙ አንድ ጊዜ ብቻ ሥልጠና ማግኘታቸውን እና የተሰጠው ሥልጠናም በጅምላ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ ስለሙዚየሙ እያሰቡ እንዳልኾነም ተናግረዋል። ማር በጥራት ስለሚያመርቱ እርሳቸው የገበያ ችግር ባያጋጥማቸውም ለሌሎች ማር አምራቾች ግን ሙዚየሙ እገዛ ቢያደርግ ፍላጎታቸው እንደኾነ አቶ ወንድምነው ገልጸዋል።

የላሊበላ ብሔራዊ የንብ ሃብት ሙዚየም ሥራ አሥኪያጅ ሲሳይ ደጀን ሙዚየሙ የተቋቋመባቸው ዓላማዎች ሲገልጹ፦
👉 በንብ ሃብት ላይ ጥናትና ምርምር ለድረግ፣
👉 የንብ እርባታ ጣቢያ በመመሥረት ሥልጠና ለመስጠት፣
👉 በሀገሪቱ ያሉ ባሕላዊ የማናቢያ ቁሳቁስ በማሠባሠብ ታሪኩን መዘከር እና ማስታወስ
👉 አረንጓዴ ግብርናን በመፍጠር፣ የቱሪዝም ምጣኔ ሃብትን በማሳደግ እና አካባቢውን በማስተዋወቅ የገቢ ምንጭ ማድረግ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ሥራ አሥኪያጁ በንብ ማነብ ሥራ ላይ ለተሰማሩትም ተግባራዊ ሥልጠና የመስጠት፣ እና ለንብ ተስማሚ የኾነውን ተክል የማልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ይሁን እና ከተቋቋመለት ዓላማ አኳያ ያልተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ሥራ አሥኪያጁ ለሙዚየም ጋላሪው የማነቢያ እና የማር ማምረቻ ቁሳቁስ መሠብሠብ እንዲሁም ማርን አቀነባብሮ ወደ ውጪ መላክ እንዳልተቻለ ነው የገለጹት። ለዚህም የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት፣ የሰሜኑ ጦርነት እና የበጀት እጥረትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ሙዚየሙ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት የበጀት፣ የቁሳቁስ እና የባለሙያ እጥረት መሙላት እንደሚያስፈልግ ሥራ አሥኪያጁ ጠቁመዋል። በአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ ሙዚየሙ የተገነባው እና ባለቤቱም የአማራ ክልል መኾኑን ገልጸዋል። ነገር ግን በሀገር ደረጃ ከፍ ያለ የምርምር፣ የኤክስቴንሽን እና የሥልጠና አገልግሎት እንዲሰጥ እየታሰበ ነው ብለዋል።

ለሙዚየሙ የተጠየቀው 18 የሰው ኀይል ተፈቅዶ ሥራ መጀመሩን እና የሰሜኑ ጦርነት ሲከሰት ሕወሓት የጦር ካምፕ አድርጎት በመቆየቱ ጉዳት እንደደረሰበት ጠቅሰዋል። አሁንም ያለው አለመረጋጋት ሠራተኞች በቦታው ተረጋግተው እንዳይቀመጡ ማድረጉን ገልጸዋል። በዚህ ምክንያትም “መሥራት በሚገባን ልክ እየሠራን አይደለም” ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

ሙዚየሙን በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርምር ማዕከል ለማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተጠና ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለጊዜው የተወሰነ የሰው ኀይል ተቀጥሮ እየሠራ ነው ብለዋል። ለጊዜው ከንብ ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል። ሙዚየሙን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት አደራጅቶ የሰው ኀይል እና ቁሳቁስ ለማሟላትም እየተከናወነ ያለው ጥናት ወሳኝ እንደኾነ ነው አቶ መኳንንት የተናገሩት። እስከዚያው ድረስ ግን የቀሰም ዕጽዋትን የማልማት፣ የሥልጠና ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

ሙዚየሙ የደረሰበትን ጉዳት ያክል ባይኾንም መልሶ ለማቋቋም በሰቆጣ ቃል ኪዳን ድርጅት ድጋፍ እየተደረገለት እንደኾነ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአፈ ጉባኤዎች የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬምን እየጎበኙ ነው።
Next articleየሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን መተግበር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተጠናቅቆ ለውይይት ዝግጁ መኾኑ ተገለጸ።