የእንጅባራ ከተማን እድገት የሚመጥን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለመገንባት እየተሠራ ነው።

13

እንጅባራ: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማ አሥተዳደሩ ”ጽዱ እና ውብ ከተሞችን በመፍጠር የአከባቢ ብክለትን እንከላከል” በሚል መሪ ሃሳብ የጽዳት ዘመቻ ተጀምሯል። የጽዳት ዘመቻውን ያስጀመሩት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ እንጅባራ ከተማ በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ ከተማ ብትኾንም የቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓቷ እድገቷን የማይመጥን መኾኑን ተናግረዋል።

“በዘመቻ በሚደረግ ጽዳት የከተማዋን ውበት የተሟላ ማድረግ አይቻልም” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ኅብረተሰቡን የከተማው ጽዳት ባለቤት ለማድረግ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ሰፊ የማኀበረሰብ ንቅናቄ እየተደረገ እንደኾነም ገልጸዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ዘላቂ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለመገንባት ደረቅ ቆሻሻን ወደ ገቢ ለመቀየር የቀረቡ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

የጽዳት ዘመቻው ተሳታፊዎችም በዘፈቀደ የሚወገደው ቆሻሻ ኅብረተሰቡን ለከፍተኛ የጤና መታወክ እየዳረገ በመኾኑ ከዘመቻ ያለፈ ሥራ የሚጠይቅ እንደኾነ ገልጸዋል። “የከተማ ውበት የሰፈሮች እና የመንደሮች ጽዳት ድምር ውጤት ነው” ያሉት ነዋሪዎቹ አከባቢያቸውን ለማጽዳት ያላቸውን ዝግጁነትም ገልጸዋል።

በጽዳት ዘመቻው የመንግሥት ሠራተኞች፣ የከተማው ነዋሪዎች እና የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ ምክክር እና መሰረታዊ ባሕሪያቱ
Next articleአፈ ጉባኤዎች የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬምን እየጎበኙ ነው።