
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የዓለም አካባቢ ቀን ”የተጎዱ የመሬት ገጽታዎችን በማገገም እና የበረሃማነት መስፋፋትን በመግታት ድርቅን የመቋቋም አቅም እንገንባ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው። የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጋሻው እሸቱ አካባቢያን መጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድም ማስተላለፍ ጭምር ነው፤ ካልተጠበቀ ደግሞ ጉዳቱ እየተባባሰ የሚሄድ ነው ሲሉ ገልጸዋል። የአካባቢ ቀን በአማራ ክልልም ከብክለት መከላከል ሥራ ጋር በማቀናጀት የአካባቢ ጥበቃ፣ የጽዳት፣ የተፈጥሮ ሃብት እና የመሬት ማገገም ሥራዎችን በመሥራት እየተከበረ መኾኑ ነው አቶ ጋሻው የገለጹት።
ጣና ሐይቅን በማጽዳት እንዲሁም ፕላስቲክን መልሶ በመጠቀም ላይ የተሠማሩ ወጣቶችን በመጎብኘት ከስድስት ወር ዘመቻ ጋር ተቀናጅቶ እየተሠራ ነውም ብለዋል። የዓለም አካባቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ ተጨማሪ ሥራዎች ቢሠሩም ባለሥልጣኑ ዓመቱን ሙሉ የሚሠራቸው ሥራዎችም የዚሁ አካል መኾናቸውን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በዋናነት በአራት የአካባቢ ጥበቃ ዓላማዎች ላይ ይሠራል ብለዋል ዳይሬክተሩ። እነሱም:-
👉 የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች፣ ፋብሪካዎች እና አገልግሎቶች በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይኖራቸው እና ብክለት እንዳይፈጥሩ መከላከል እና መቆጣጠር፣
👉 በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ደኖች እንዲጠበቁ፣ የደን ሕጋዊ አጠቃቀም እንዲኖር እና ወጣቶች ተደራጅተው እንዲያለሙ ማድረግ፣
👉 ብሔራዊ ፓርኮች እና የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎች ይዞታቸው የተከበረ፣ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው እና የሚጠበቁ ኾነው ለቱሪዝሙ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማልማት እና
👉 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ምጣኔ ሃብት በመገንባት ማኅበረሰቡ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እንዳይደሥስበት ማድረግ ለዚህም ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር ተባብሮ መሥራት መኾናቸውን ገልጸዋል።
አገልግሎት ሰጪ እና አምራች ተቋማት የካርበን ልቀትን እና በአየር ንብረት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮችንም አቅደው እንዲሠሩ ተቋሙ እያስተባበረ መኾኑንም አቶ ጋሻው ጠቅሰዋል።
የአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ሲዳከም የበረሃማነት መስፋፋት፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የእንስሳት ጤና ማጣት እና ስደት፣ ሌሎችም ጉዳቶች ይከሰታሉ ያሉት አቶ ጋሻው የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ አሳሳቢ እና ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚሻ መኾኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ተሰጥቶት በአረንጓዴ አሻራ የደን ልማት ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በከተሞችም የጽዳት እና ውበት ሥራ እና የአካባቢ ብክለትን የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አመላክተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ”ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ቃል የሚከወነውን የብክለት መከላከል ዘመቻ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤታቸውም ተቀላቅሎ እየሠራ መኾኑን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። የክልሉ ከፍተኛ መሪዎችም በትኩረት በየደረጃው ከሚገኝ መዋቅር እና ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ የጽዳት ዘመቻውን እየተገበሩ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ጽዳትን ባሕል እንዲያደርግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የማኅበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር የአካባቢ ጥበቃ ባሕል የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የጠቀሱት አቶ ጋሻው ለዚህም በሚያዝያ የፕላስቲክ፣ በግንቦት የአየር፣ በሰኔ የአፈር፣ በሐምሌ የድምጽ ብክለቶችን እንዲሁም በነሐሴ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማን በየወራቱ በመርሐ ግብር እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ከተሞች እና ቀበሌዎችም እንደየአካባቢያቸው የየራሳቸውን ሥራ በመሥራት የአካባቢ ጥበቃ ቀንን እያከበሩ መኾኑን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ለአካባቢ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እና አሳሳቢ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ሥራው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ ”ለዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል” በማለት ሥራው የአንድ ተቋም ብቻ ስላልኾነ ሁሉም አካል ለአካባቢ ጥበቃ በትኩረት እንዲሠራ እና እንዲተባበር አሳስበዋል።
ለአካባቢ ጥበቃ እየተሠራ ያለው ሥራ በቂ አይደለም፤ ጅምር ለውጦችን አጠናክሮ በመቀጠል እንሠራለን፤ ኅብረተሰቡም ተባባሪ እና አስቦ የሚሠራ መኾን አለበት ያሉት አቶ ጋሻው ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በማኅበረሰቡ በማስረጽ እና ባሕል በማድረግ መኾኑን ጠቅሰዋል። ለዚህም ግንዛቤ የመፍጠር፣ የተግባር ዘመቻዎቹን አጠናክሮ የመቀጠል እና ውጤቶቹን እየገመገሙ የመሥራትን አስፈላጊነት አመላክተዋል።
የዓለም አካባቢ ቀን በአማራ ክልል ለ27ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ31ኛ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ51ኛ ጊዜ ተከብሯል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!