“የጸጥታ ችግር የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል” የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ

36

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን 232 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ነበር። እስከ ግንቦት አጋማሽ ከ609 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ወጣት ስማቸው እሸቴ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ ውስጥ የሥራ እድል ተጠቃሚ ከኾኑት ውስጥ አንዱ ነው። ወጣቱ በ2015 ዓ.ም ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ቢመረቅም ለ10 ወራት ያህል ያለሥራ እንደቆየ ነግሮናል። የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት በ2016 በጀት ዓመት ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሽርክና ማኅበር በማደራጀት በከተማው የሚሠሩ መሠረተ ልማቶችን እንዲያከናውኑ አድርጓል። በሚያገኘው ገቢም ቤተሰቡን እያሥተዳደረ ይገኛል፡፡

የእንጀባራ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የቆየ ጥላሁን እንደገለጹት በ2016 ዓ.ም 8 ሺህ 463 ዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በዘጠኝ ወራት 2 ሺህ 343 ለሚኾኑት የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 526 የሚኾኑ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው። የሰላሙ እጦት ደግሞ ዕቅዱን ለማሳካት ፈተና መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ወጣቶች በከተማ አገልግሎት፣ በአምራች ዘርፍ፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድ ዘርፍ እና በኮንስትራክሽን ላይ እንዲሰማሩ መደረጉንም ገልጸዋል። በዘጠኝ ወሩ ለ265 ሥራ ፈላጊዎች 20 ሚሊዮን 235 ሺህ 349 ብር የተዘዋዋሪ ብድር ማስተላለፍ ተችሏል ብለዋል። ከተሰራጨው ተዘዋዋሪ ብድር ደግሞ 99 በመቶ መመለስ ችለዋል፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ 5 ዓመት እና ከዚያ በላይ የተያዙ የመሥሪያ ኮንቴነሮችን ለአዲስ ተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ወራት አዳዲስ ሥራ ፈላጊዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የ100 ቀን ዕቅድ በማስቀመጥ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከታቀደው ከ1 ሚሊዮን 232 ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ ከ609 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ከዚህ በፊት ለአሚኮ መግለጻቸው ይታወሳል። የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ውስጥ 62 ሺህ የሚኾኑት በውጭ ሀገራት የተፈጠረላቸው ናቸው። ከተሞቹ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ እና ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ አቅርበዋል።

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና በሥራ ላይ ያሉትንም ለመደገፍ እንቅፋት ማጋጠሙን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን ብለው ነበር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር። ቃል በተግባር እየተፈጸመ መሆኑን ትናንት ባደረግነው ጉብኝት አረጋግጠናል። ሰፋፊ ጎዳናዎች፣ ምቹ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ አረንጓዴ አካባቢ፣ ንጹሕና ዘመናዊ የመጸዳጃ ቤቶች፣ የተግባቡና የተዋቡ የግንባታ መልኮች፣ አዲስ አበባን እየቀየሯት ነው።
Next article”ለዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል” የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን