
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በታች አርማጭሆ ወረዳ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ያለመ የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል። በምክክር መድረኩ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኃይለማርያምን ጨምሮ ሌሎች የዞን ከፍተኛ አመራሮችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የታች አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስማረ የኋላሸት አሁን ላይ በወረዳው ያለውን አንፃራዊ ሰላም ተከትሎ ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር ሕግ የማስከበር ሥራ በስፋት እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ከሰሞኑ ከ100 በላይ የሚኾኑ ፅንፈኛ ኃይሎች የሄዱበት አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን በመገንዘብ እና መንግሥት ያመቻቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደየቤተሰቦቻቸው እየተቀላቀሉ እንደሚገኙ ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በዚህ የርስበርስ ግጭት የአማራ ሕዝብ በኢኮኖሚና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲጎሳቆል ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰው ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
“እርስ በእርስ እያጋጩ ችግር የሚፈጥሩትን ኃይሎች ሁላችንም መታገልና ማውገዝ ይኖርብናል” ያሉ ሲሆን ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሰፍን በንቃት እንደሚሳተፉም አረጋግጠዋል።
በተለያየ ምክንያት በጫካ ለቆዩና የሰላም አማራጩን መርጠው እየተቀላቀሉ ላሉ ታጣቂዎችም መንግሥት የመሥሪያ ቦታና ብድር ከማመቻቸት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምሳል አመረ በመልዕክታቸው ዘላቂ ሰላምን በማፅናት የሕዝባችንን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያው ተጠቃሚነቱን ማሳደግ ይገባናል ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም በአሁኑ ሰዓት በዞኑ የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታትና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል ሁሉም አካል ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይ እያጋጠሙ ያሉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና ልማት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ደግሞ ሰላም ዋነኛ መሠረት መሆኑን በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጠዋል።
በመሆኑም መላው ሕዝብ የተጀመረውን ሰላም በዘላቂነት በማጽናት፣ የሕግ የበላይነትን በማስፈን እና አስተማማኝ ሰላም በመፍጠር በኩል ከአመራሩ እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!