“በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ሥራዎች ሀገሪቱ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ጉልበት ናቸው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

30

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ ውይይት በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ነው የተካሄደው።

መድረኩን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ፣የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በጋራ የመሩት ሲኾን በውይይቱ ላይ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳታፊ ኾነዋል።

ለውይይቱ እንደ ሀገር አቀፍ የተዘጋጀውን መነሻ ጹሑፍ ያቀረቡት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ለኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና ራስን መቻል የዚህ ዘመን አርበኝነት ማረጋገጫ መኾኑን ተናግረዋል።

በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሃሳቦች ማብራሪያ የሰጡት አረጋ ከበደ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ሥራዎች ሀገሪቱ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ጉልበት መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ጉዞ መሳካት ሁሉም ለሰላም፣ ለወንድማማችነት እና ለአብሮነት ቅድሚያ በመስጠት የሀገር አንድነት እና ሉዓላዊነትን በጽኑ መሠረት ላይ መገንባት አለብን ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የውይይቱ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘውን መሠረታዊ ለውጥ በዘላቂነት በማስቀጠል በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ማማ የማድረስ ሀገራዊ ራዕይን እውን ለማድረግ ከከተማ አሥተዳደሩ ጎን በመቆም በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል::

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ወሎ ዞን የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች በሕወሓት እየተፈጸመ ያለውን ግፍ በሕዝባዊ ሰልፍ ገለጹ።
Next article“እርስ በእርስ እያጋጩ ችግር የሚፈጥሩትን ኃይሎች ሁላችንም መታገልና ማውገዝ ይኖርብናል” የታች አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪዎች