
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደራል፣ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ በበጀት ዓመቱ የተጠናቀቁ እና እየተሠሩ ያሉ የካፒታል በጀት ኘሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
የሃና መኳት ጤና ጣቢያ የእናቶች ክትትል እና ማዋለጃ ክፍል ተጨማሪ ግንባታ በአልማ እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በ90 ቀናት ውስጥ ተሠርቶ መጠናቀቁን የመቄት ወረዳ አስተዳዳሪ አወቀ ደሳለኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ወደ ጤና ጣቢያው የሚወስደውን 17 ኪሎሜትር መንገድ የወረዳው አሥተዳደር ከሕዝቡ ጋር በመተባበር በ7 ሚሊየን ብር እንዲጠገን አድረጓል ነው ያሉት።
134 ሚሊየን ብር በጀት የተያዘላቸው 43 ኘሮጀክቶች በተያዝነው በጀት ዓመት እየተሠሩ መኾናቸውን አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
በክልል መንግሥት በጀት የሚሠሩ የገጠር መንገዶችም የጉብኝቱ አካል ነበሩ።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አራጌ ይመር ወረዳው የሠራቸው የልማት ኘሮጀክቶች አፈጻጸም አበረታች ነው ብለዋል። ዞኑም ለአፈጻጸማቸው ስኬት ክትትልና ድጋፍ ያደርግ ነበር ነው ያሉት።
የንጹህ መጠጥ ውኃ ጥያቄ ያላቸውን ቀበሌዎች የውኃ ምንጭ በማስጠናት ለክልል እና ለረጅ ድርጅቶች ለማቅረብ ዞኑ እየሠራ ነው ብለዋል።
ኘሮጀክቶችን ገጠር ድረስ እየደገፉ መሥራት እና በወቅቱ ማጠናቀቃቸው የሚያስደንቅ ነው ያሉት የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኅላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር.) በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ ኘሮጀክቶችን በታቀደለት ጊዜ መፈጸም የፓርቲውን የመፈጸም አቅም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንገሥትም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ካሳሁን ኀይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!