“ያለንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በአግባቡ ለይተን የሞት ሽረት ትግል በማድረግ እራሳችንን ከልመና በማውጣት ክብራችንን ማስጠበቅ አለብን” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

22

ደብረ ብርሃን: ሰኔ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተረጂነት አስተሳሰብ በመውጣት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ ውይይት በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኅላፊ እና የብልጽጋና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር) ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የኾኑ አደጋዎች ባጋጠሙ ጊዜ ለልመና እጃችንን ስንዘረጋ ቆይተናል ብለዋል።

ይኽ የሚኾነው ደግሞ ማልማት የሚያስችል አፈር፣ ውኃ፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና መሥራት የሚችል የሰው ኀይል ባለበት ነው ብለዋል።

ይሄ ደግሞ በታሪክ በቅኝ ያለመገዛታችንን ያኽል በተቃራኒው በእርዳታ ሰበብ ሉዓላዊነታችን እና ነጻነታችንን እንዲፈታተኑት አድርጓል ነው ያሉት።

ይኽንን ታሪክ መቀየርና በምግብ ራስን በመቻል ሉዓላዊነታችንን ማስከበር ይኖርብናል ብለዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ስር የሰደደውን የልመና እና ተረጂነት ስሜትን በቅድሚያ ማስወገድ ይገባል ብለዋል።

በዚያው ልክ የራስን ችግር በራስ አቅም የመፍታት አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለልመና የሚዳርጉን ቢኾንም አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥሪት አለማካበታችን ደግሞ የበለጠ እንድንቸገር ምክንያት ኾኗል ነው ያሉት።

ያለንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በአግባቡ ለይተን የሞት ሽረት ትግል በማድረግ እራሳችንን ከልመና በማውጣት ክብራችንን ማስጠበቅ አለብን ብለዋል ዶክተር አሕመዲን።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ከተረጂነት ለመውጣት በሌማት ትሩፋት እና በሌሎችም የልማት ፕሮግራሞች እየተሠራ ቢኾንም በቂ ባለመኾኑ ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ለዓለም ለይኩን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝቡ ታጥቀው ወደ ግጭት የገቡ ወገኖች ወደ እርቀ ሰላም እንዲመለሱ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next article“በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ ኘሮጀክቶችን በእቅድ መፈጸም የፓርቲውን የመፈጸም አቅም የሚያሳይ ነው” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር.)