“ሕዝቡ ታጥቀው ወደ ግጭት የገቡ ወገኖች ወደ እርቀ ሰላም እንዲመለሱ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

13

ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢው የጸጥታ ጉዳይ ላይ ከክልሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቸና ከተማ በአካባቢው ሰላምን በማምጣት ሕዝቡን ወደ ቀደመ የተረጋጋ ሕይወቱ ለመመለስ ዓላማ ያደረገ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ የተሳተፉ የቢቸና ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች እርቀሰላም ይውረድ እርስ በርሳችን መገዳደል ይብቃ ሰላማችን ይመለስ መንግሥት በሕዝቡ የሚነሱ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ነጻነትን ጨምሮ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በጊዜ ይፍታ ብለዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በዞኑ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አጥፊዎችን መክረው ወደ ሰላም መንገድ እንዲመልሱ ጠይቀዋል።

አሥተዳዳሪው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችም የታየው አንፃራዊ ሰላም ወደ ሁሉም የዞኑ አካባቢዎች እንዲሰፋ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

ከነዋሪዎች ጋር የመከሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ፈተና ቢኾንም እስከ ግንቦት ማብቂያ ድረስ ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሮች መቅረቡን ገልጸዋል።

ሕዝቡም ታጥቀው ወደ ግጭት የገቡ ወገኖች ወደ እርቀ ሰላም እንዲመለሱ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በውይይቱ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሠብሣቢ አስቻለ አላምሬ ግጭቱ እንዲቀጥል እና ሕዝቡ ተረጋግቶ ሕይወቱን እንዳይመራ የሚሠሩ ኀይሎችን በጋራ እንታገል ብለዋል።

በምዕራብ እዝ የ403 ኮር አዛዥ እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብርጋዴል ጀኔራል አዘዘው መኮንን ማኅበረሰቡ ሰላሙን ከሚያሳጡ የተዛቡ መረጃዎች እራሱን እንዲጠብቅ እና አጥፊዎችንም እንዲያርም አሳስበዋል።

በመድረኩ የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ አለመግባባቶች በውይይት እና በይቅርታ ሊፈቱ እንደሚገባም መግባባት ላይ ተደርሷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳምንቱ በታሪክ
Next article“ያለንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በአግባቡ ለይተን የሞት ሽረት ትግል በማድረግ እራሳችንን ከልመና በማውጣት ክብራችንን ማስጠበቅ አለብን” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)