ሳምንቱ በታሪክ

47

👉የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምሥረታ

ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥር ከሚታተሙት ዕለታዊ ጋዜጦች መካከል አንዱ የኾነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሕትመት የጀመረው የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በስደት ከቆዩባት እንግሊዝ ሀገር ከተመለሱ ከአንድ ወር በኋላ ነበር፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ በድል አድራጊነት መንፈስ ከስደት የተመለሱት ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመታት በወረራ ይዞ የነበረው ጣሊያን ተሸንፎ ከሀገር መውጣቱን ተከትሎ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመጀመሪያው ዕትሙ አንድ ትልቅ ፎቶ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡

ይህ ፎቶ ንጉሡ በአውቶሞቢል በክብር ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ ያሳያል፡፡ ከዚህ ባለፈም የጋዜጣው የመጀመሪያው ዕትም የዜና ርእሱ “የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር” ይል ነበር፡፡

“ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ኢትዮጵያውያን የረዳትነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ ተመሠረተ“ የሚለው ደግሞ የጋዜጣው የመጀመሪያ ዜናው መሪ አንቀጽ ነበር፡፡

ጋዜጣው “አዲስ ዘመን” የሚለውን ስያሜ ያገኘው ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገቡ ከተናገሩት ንግግር ጋር የተያያዘ እንደኾነ የጋዜጣው የመጀመሪያ ዕትም ያሳያል፡፡

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከስደት ከቆዩበት እንግሊዝ ተመልሰው አዲስ አበባ ሲገቡ ባደረጉት ንግግር “ከማናቸውም አሥስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መኾኑን ነው፡፡ በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል“ ብለው ስለነበር ጋዜጣውም “አዲስ ዘመን“ ተብሎ እንደተሠየመ ይነገራል፡፡

ኢ.ፕ.ድ እንዳስነበበው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዚህ ሳምንት ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ ሕትመቱ ሳይቋረጥ እስከዛሬ ድረስ እየታተመ ለአንባቢያን በመድረስ ላይ ነው፡፡

👉የጳውሎስ ኞኞ ሕልፈት

ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም በምሥራቅ ሐረርጌ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ ተወለዱ፡፡ ዕድገታቸው ግን ድሬዳዋ ነው፡፡

እናታቸው ወይዘሮ ትልጫለሽ አንዳርጌ ይባላሉ፡፡ አባታቸው ደግሞ አቶ ኞኞ የተባሉ ግሪካዊ ነጋዴ ነበሩ፡፡

ጳውሎስ የመጀመሪያ ስማቸው አማረ ነበር፡፡ ሁለተኛው ዙር የኢትዮ -ጣሊያን ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ድሬዳዋ ውስጥ የቀለም ትምህርታቸውን ጀመሩ፡፡ በትምህርት አቀባበላቸው ፈጣን እና ጎበዝ ስለነበሩ በእጥፍ እያለፉ አራተኛ ክፍል ደረሱ፡፡

እናትና አባታቸው አብረው አይኖሩም ነበርና እናታቸው ችግር ውስጥ ገብተው ስለነበር ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም፡፡ በመኾኑም ጳውሎስ ትምህርታቸውን ከአራተኛ ክፍል አቋርጠው እናታቸውን በሥራ ለማገዝ ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡

ጳውሎስ 17 ዓመት ሲኾናቸው በእርሻ ሚኒስቴር ሥር ወደ ሐረርጌ ክፍለሀገር ጨርጨር አውራጃ ሄደው ተቀጠሩ፡፡ በወርም 8 ብር ይከፈላቸው ነበር፡፡ በዚህ ሥራቸው ሦስት ዓመት አካባቢ ከቆዩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል በጸሐፊነት ተቀጠሩ፡፡ ደመወዛቸውም ወደ 80 ብር እንዳደገላቸው በጳውሎስ ኞኞ ግለ-ታሪክ መጽሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡

የጽሑፍ ሥራቸውን አሳድገውም ለተለያዩ ጋዜጦች መላክ ጀመሩ፡፡ ጹሑፎቻቸውንም በጋዜጣ ማሳተም ከቀጠሉ በኋላ የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ጠራቸው፡፡

በኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡

የጋዜጣዋን ይዘት ቀይረው በአንባቢ ዘንድ በጉጉት የምትጠበቅ አድርገዋታል፡፡ ጋዜጣ አዟሪዎችንም መልምለው አንድ አይነት የደንብ ልብስ አሰፉላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ አዟሪ ብቻ እንዲኾኑ አድርገው ጥሩ የኾነ የገበያ ሥርዓት ዘረጉ፡፡

በዚህ ሁሉ ሥራ በዓመት 1ሺህ ጋዜጣ ብቻ ለማሳተም ዕቅድ የሰነቀችው የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ በሂደት እስከ 30ሺህ ጋዜጣ ትታተም ጀመር፡፡ ጳውሎስ ከኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ከወጡ በኋላ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ሥራ ጀመሩ፡፡

በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጳውሎስ ያዘጋጁት የነበረው ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ›› የሚለው አምድ ልዩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቪዥንም ሠርተዋል፡፡

ጳውሎስ በጋዜጠኝነት ሕይወታቸው ውስጥ ሙያቸውን ለማዳበር በቼኮዝላቫኪያ፣ ሶቪየት ኅብረት እና ሃንጋሪ በመሄድ ልምድ ቀስመው ተመልሰዋል፡፡

ሐብታሙ ግርማ ደምሴ በ2011 ዓ.ም “ጳውሎስ ኞኞ እና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው” በሚል ባሳተሙት ጽሑፍ እንዳተቱት ጳውሎስ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ታሪክ ተመራማሪ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድም በርካታ መጽሐፍትን ጽፈው አሳትመዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት፣ አጤ ሚኒሊክ፣ አጤ ቴዎድሮስ፣ አጤ ሚኒሊክ ከውጪ ሀገራት ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ አጤ ሚኒሊክ በሀገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ የአጤ ዮሃንስ ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢንሳይክሎፒዲያ የሚባሉትን መጽሐፍትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሳይታተሙ የቀሩ በርካታ መጽሐፍት ነበሯቸው፡፡

ጳውሎስ ከታሪክ ጸሐፊነታቸው ባሻገርም ልቦለድም ይጽፉ ነበር፡፡ ያሳተሟቸው የልቦለድ መጽሐፍትም አሉ፡፡ የጌታቸው ሚስቶች፣ የኔዎቹ ገረዶች፣ የአራዳው ታደሰ፣ ከሴቶች አንባ፣ እንቆቅልሽ፣ ምስቅልቅል፣ ቅይጥ የሚሉት መጽሐፍት ይጠቀሱላቸዋል፡፡ ሌሎች ኢ-ልቦለድ መጽሐፍትም ነበሯቸው፡፡

“ችግር ሥር ከሰደደ መዘዙ ብዙ ነውና በጋራ ኾነን በእንጭጩ እንቅጨው” የሚል መርህ ያላቸው ጳውሎስ በልቦለድ ሥራዎችም ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ያሳዩ ነበር፡፡

የ1983ቱ መንግሥት ለውጥ እንደመጣ ‹‹ሩህ›› የምትባል የግል መጽሔት ዋና አዘጋጇ ኾነው እየሠሩ ሳለ በመታመማቸው በጀርመን እና አሜሪካ ሄደው ታከሙ፡፡ ነገር ግን ህመሙ ጸንቶባቸው በዚህ ሳምንት ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ሕይወታቸው አለፈ፡፡

👉 “ግንቡን አፍርሱት!”

40ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን እና የሶቪየት ኅብረት ኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ እንዲሁም የሀገሪቱ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ ምሥራቅ ጀርመን ብራንደንበርግ “በር” (በርሊን ከተማ አጠገብ) የተገናኙት በዚህ ሳምንት ነበር፡፡

የበርሊን ግንብ ካፒታሊስቷን ምዕራብ ጀርመን ከሶሻሊስቷ ምሥራቅ ጀርመን የሚነጥል የኮንክሪት መከላከያ ግንብ ነው፡፡ “የሞት ንጣፍ” በመባልም ይጠራል፡፡

ናሽናል ጅኦግራፊክ በድረ ገጹ እንዳስነበበው ግንቡ 155 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡ ግንቡ ሰዎች ከምሥራቅ ጀርመን ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዳይሄዱ የሚያደርግ ነበር፡፡

ግንቡ የአልሙኒየም ቅብ ስለነበረው እንደ አደገኛ የኤሌክትሪክ አጥርም ኾኖ ያገለግላል፡፡ ሰዎች ወደ ምዕራቡ ዓለም ለመሸሽ ሲሞክሩም ስለተገደሉ የግንብ አጥሩ “የሞት ንጣፍ” የሚል ስያሜ እንዲሰጠው አድርጓል፡፡

ግንቦት እና የበርሊን ግንብ እጣ ፋንታ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን እና የሶቪየት ኅብረት አቻቸው ሚካኤል ጎርባቾቭ የተገናኙት ስለበርሊን ግንብ ጉዳይ ለመነጋገር ነበር፡፡ ሬገን በመጀመሪያ እንዲናገሩም እድል ተሰጣቸው፡፡

” የተከበሩ ሚካኤል ጎርባቾቭ ከኋላዬ የበርሊንን ከተማን ነፃ እንቅስቃሴ የሚገድብ ግንብ ቆሟል፡፡ ግንቡ በአጠቃላይ የአውሮፓን አህጉር የሚከፋፍል የአጥር ሥርዓት አካል ነው። ይህ ግንብ ፈርሶ የሰው ልጆች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መሥራት አለብን፡፡ ጎርባቾቭም ይህን በር ክፈቱ! ሚስተር ጎርባቾቭ!
ይህን ግድግዳ አፍርሱ!”ሲሉ የተናገሩት በዚህ ሳምንት ግንቦት 25 ቀን 1987 ነበር፡፡

እንደተባለውም አሜሪካ የሶቪየት ኅብረት እጅ ስለተጠመዘዘ የበርሊን ግንብ ፈረሰ፤ የሶሻሊስት ሥርዓትም ተንኮታኮተ፤ በሂደትም የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት ተበታተኑ፡፡ ኅያሏ ሶቪየት ኅብረትም ፈራረሰች፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥበባት መጪውን ትውልድ ቅርጽ በማስያዝ እና የከተማችንን የቱሪዝም መስሕብ በማላቅ ከፍ ያለ ሚና ይጫወታሉ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ሕዝቡ ታጥቀው ወደ ግጭት የገቡ ወገኖች ወደ እርቀ ሰላም እንዲመለሱ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)