“አስከፊ ከኾነው የተመፅዋችነት እሳቤ የምንወጣበት ነባራዊ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

27

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ሀገሪቱን ከተረጂነት ለማውጣት የቀየሰውን ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ገልጸዋል።

የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ መሪዎች በምዕራብ አርሲ ዞንና በሻሸመኔ ከተማ የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አብዱ ሁሴን አስከፊ ከኾነው የተመፅዋችነት እሳቤ የምንወጣበት ነባራዊ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል።

ዛሬ የሁለቱ ክልሎች የሥራ ኀላፊዎች በምዕራብ አርሲ ዞን ያደረጉት ጉብኝት ይህንን አላማ ለማሳካት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለመጎብኘት መኾኑን አብራርተዋል።

በምዕራብ አርሲ ዞን እና በሻሸመኔ ከተማ ያየናቸው የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ከተረጂነት ወደ ተሟላ ምርታማነት ለመግባትና የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር የሚያስችሉ መኾናቸውን አይተናል ብለዋል።

መርሐ ግብሩ ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር በዘለለ ለአካባቢው ሕዝብ ሰፊ የወተት ሀብት እንዲቀርብ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም አስረድተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አቡዱልሀኪም ሙሉ እንደገለፁት፤ መንግሥት ከተመፅዋችነት የመውጣት አቅጣጫን በመቀየስ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

እውነተኛ ሉዓላዊነት እና ነጻነት መምጣት የሚችለው በምግብ ሰብል እራሳችንን ስንችልና ከተረጂነት በመላቀቅ ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን ስንገነባ ነው ብለዋል።

የኢኮኖሚ አቅማችንን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያሉንን የተፈጥሮ ጸጋዎች ከሰፊ ሃብት ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።

በተለይ የተከበረ ሀገርና ሕዝብ የሚኖረን ያለንን አቅም ተጠቅመን መለወጥ ስንችል ነው ያሉት አቶ አብዱልሀኪም ከኋላ ቀርና ከድህነት ለመላቀቅ ርብርብ ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው አሁን ላይ ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ መጠቀም የሚያስችሉ ዕቅዶች ወርደው እየተተገበሩ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በጉብኝቱ በምዕራብ አርሲ ዞን ወንዶ ወረዳና በቢሻን ጉራቻ ከተማ የወተትና የእንስሳት እርባታ፣ የእንቁላልና የስጋ ዶሮ እርባታ፣ የከተማ ግብርናና የፍራፍሬ ችግኝ ብዜትና ልማት ስራዎች ምልከታ ተደርጓል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላም እጦቱ ከዚህ በላይ እድሜ እንዳያገኝ ማድረግ አለብን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next article875 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።