“የሰላም እጦቱ ከዚህ በላይ እድሜ እንዳያገኝ ማድረግ አለብን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

24

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

ውይይቱን የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ተስፋዬ ይገዙ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው መርተውታል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የሰላም ባለቤት እኛው መኾን አለብን፣ እኛ ምን ጎድሎን ነው ከሌሎች ሰላምን የምንጠብቅ? ብለን ራሳችን መጠየቅ አለብን ነው ያሉት።

“የሰላም እጦቱ ከዚህ በላይ እድሜ እንዳያገኝ ማድረግ አለብን” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከዚህ በላይ እድሜ ካገኘ ጉዳቱ መጠነ ሰፊ ነው ብለዋል።

የልጆቻችንን እድሜ አንድ ዓመት ወደኋላ መልሰናል፣ ቀውሱ ማንንም አልጎዳም፣ የጎዳው እኛኑ ነው፣ ከመሪ እስከ ተመሪ ድረስ እርስ በእርሳችን ተገዳደልን፣ ይሄ ደግሞ በእጅጉ ጎድቶናል እንጂ ለውጥ አላመጣም ብለዋል።

ሰላም የሁሉም መሠረት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተጀመረውን ሰላም ዘላቂ ማድረግ የመንግሥት እና የሕዝብ ድርሻ መኾኑን አመላክተዋል።

በግጭቱ ምክንያት የሕዝቡ ማኅበራዊ ትስስር በእጅጉ እየተጎዳ መኾኑንም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ወንድሞች ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው መንግሥት ችግርን በውይይት ለመፍታት ሁልጊዜም ዝግጁ መኾኑን ተናግረዋል።

አሁን የችግር መፍቻ መንገድ አይደለም የቸገረን፤ የመፍቻ መንገዱን መቀበል ላይ ነው የተቸገርን ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለሰላም ቁርጠኛ የኾነ አካል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ለም መሬት እና ጸጋ የበዛበት አካባቢ ይዞ ከሌሎች መጠበቅ እንደማይገባም ተናግረዋል።

በከተማዋ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በትጋት እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።

በከተማዋ ውስጥ አትክልት እና ፍራፍሬ በስፋት እንዲመረት እና ራስን ከመቻል አልፎ ሌሎችን ለመትረፍ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአሳ ምርት እና ሌሎች ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

ከመወቃቀስ ወጥተን በአንድነት እና በመደጋገፍ መሥራት ይገባልም ብለዋል።

ቀልጣፋ እና ቅን የኾነ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ እና ጠራ ወረዳ በመገኘት የአምራች ፋብሪካዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመለከቱ፡፡
Next article“አስከፊ ከኾነው የተመፅዋችነት እሳቤ የምንወጣበት ነባራዊ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን