
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከባሕርዳር ከተማ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ተስፋዬ ይገዙ፣ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ሕዝብን እያማረረ ያለውን የሰላም ችግር በውይይት መፍታት እና ለሕዝብ እፎይታ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከግጭት ወጥተን በሰላም ሠርተን የምንገባበትን ሁኔታ እንሻለንም ብለዋል።
ክልሉ ራስን ከመቻል አልፎ ለሀገር የሚጠቅም ሃብት አለው፣ ነገር ግን የሰላም እጦት አስቸጋሪ አድርጎበታል ነው ያሉት።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመከራ ጊዜያትን አሳልፈናል ያሉት ነዋሪዎቹ በመከራችን ጊዜ የሌሎች ክልሎች መሪዎች ያደረጋችሁልን ድጋፍ፣ ያሳያችሁንን አብሮነት አንረሳም ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ለልማት ቀናዒ ታታሪ እና ሠርቶ ለመለወጥ ረፍት የሌለው መኾኑንም ገልጸዋል። ከተረጅነት ለመላቀቅ አስተሳሰብ ላይ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአማራ ሕዝብ በሀገሩ ላይ ሠርቶ የሚበላበት መንገድ ሊመቻችለት ይገባል፣ በዘረኝነት አስተሳሰብ በሀገሩ ሊፈናቀል እና ሊሳደድ አይገባም ብለዋል።
ምሁራን ችግሮች ሰላማዊ በኾነ መንገድ እንዲፈቱ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
መንገዶች እየተዘጉ ሰላም እየደፈረሰ ከተረጅነት ለመውጣት አይታሰብም ብለዋል።

ራሳችን ሰላምን እንጠብቅ፣ ሰላም ከሁሉም በላይ ሕይወት እና ምግብ ነው፣ አሸናፊነት እና ተሸናፊነት የትም አያደርሰንም ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አንድነት የሚፈጠርበትን መንገድ ማስተማር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ሌሎች ክልሎች እያንዳንዷን ጊዜ ለልማት እየተጠቀሙባት ነው፣ እኛ ግን በግጭት ውስጥ እያሳለፍን ነው፣ ይሄን ማስተካከል አለብን ብለዋል።
የተረጅነት አስተሳሰብ ሕዝብን በችግር ውስጥ እንዲኖር እያደረገው መኾኑንም አመላክተዋል።
የሥራ ባሕላችንን በማስተካከል ሀገራችንን መለወጥ ይገባል ነው ያሉት።
ዜጎች ከአንደኛው አካባቢ ወደ ሌላኛው ሄደው ሠርተው እንዲበሉ የሀገሪቱ ሕጎች መሻሻል እንደሚገባቸውም ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት የተሄደበት መንገድ የተሳሳተ በመኾኑ ትርፍ አምራች የነበረው ሕዝብ እየተራበ ነው ብለዋል።
ትናንት አዲስ አበባ መግባት አንችልም እንል ነበር ዛሬ ግን ወደ ወረዳ መሄድ አንችልም፣ ጥያቄ በጦርነት አይፈታም፣ ችግራችን እንዲፈታ የክልሉን መንግሥት እናግዝ ነው ያሉት።
በጫካ የሚገኙትን በውይይት እንድትመልሱ እንዲሁም ሰላምን እንድታጸኑ እንጠይቃለን ነው ያሉት።
ወንድም ከወንድሙ ጋር መገዳደል ይበቃናል፣ ልማት ለማምጣት መገዳደልን ማቆም ፍቅርን ማጎልበት አለብን ብለዋል።
ድህነትን ለመበቀል አንድነት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
