“በእርዳታ ስም በእጅ አዙር ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚፈልጉ ኀይሎችን ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ሀገራዊ አቅምን መገንባት ያስፈልጋል” ርእሰ መሥተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ.ር)

52

ጎንደር: ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር” በሚል መሪ መልዕክት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።

በውይይቱ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ የአብሮነት ተምሳሌቷ እና መናገሻዋ ጎንደር ለኢንቨስትመንት ምቹ ከተማ ናት ብለዋል።
ከተማዋ እንድትለማ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ጠቅሰው በምግብ ራስን ለመቻልም ተግቶ የልማት ሥራዎች ላይ መሳተፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በከተማ አሥተዳደሩ ከ23 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ከድህነት ወለል በታች ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሴፍትኔት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ያነሱት አቶ ባዩህ ዜጎች ከተረጂነት እንዲወጡ የቁጠባ እና የሥራ ባሕልን ማዳበር ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በመድረኩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ክልላቸው በትጋት እንደሚሠራ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከተረጅነት እንድትወጣ አምራች ዜጋ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ማምረት፣ ጠንካራ የሥራ ባሕልን ማሳደግ እና ምቹ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
“በእርዳታ ስም በእጅ አዙር ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚፈልጉ ኀይሎችን ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ሀገራዊ አቅምን መገንባት ያስፈልጋል” ብለዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሀገር በቀል የመረዳዳት ባሕልን ማሳደግ፣ አደጋን የመቆጣጠር አቅም መገንባት፣ ልመና እና የተረጂነት ስሜትን ማስቀረት እንዲሁም የበጋ መስኖ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። ክልላዊ፣ ዞናዊ እና ከተማ አቀፍ የአደጋ ጊዜ ፈንድ ማቋቋም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

ጎንደር የአብሮነት ከተማ ናት ያሉት ደግሞ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር እርስቱ ይርዳው ናቸው።
የመልካም ታሪክ ባለቤት የኾነችውን ጎንደር ማልማት ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ኀላፊነት ነው ብለዋል።

በውይይቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋገሾ (ዶ.ር)፣ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር እርስቱ ይርዳው፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ወርቁ ኀይለማሪያምን ጨምሮ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ አዲስ ዓለማየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተናን ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁ ተገለጸ።
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን በጋሸና ከተማ የኢንቨስትመንት ፎረም እየተካሄደ ነው።