
ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚችሉ ጉዳዮች ከባሕርዳር ከተማ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ተስፋዬ ይገዙ፣ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ የክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ተባብረው መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በከተማዋ ባዩት የልማት ሥራ መደነቃቸውንም ተናግረዋል። ከተማችሁን እያስዋባችሁ እንደኾነ አይቻለሁ ነው ያሉት። እኔ የመጣሁባትም ከተማ እንደዚህ በኾነልኝ ብዬ ተመኝቻለሁ ብለዋል። በውስጡ የሚኖር ወይም ሌላ ዓላማ ያለው እየለማ ያለውን ላያየው ይችላል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል በለውጡ ዓመታት የለማውን ያክል ባለፉት ዓመታት አልለማም ማለት እንደሚቻል አስረድተዋል። በዓባይ ድልድይ፣ የጎርጎራ ፕሮጄክት እና ሌሎች የልማት ሥራዎች በክልሉ ከፍተኛ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ያመላክታል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት የተሟላ ሰላም አግኝቶ ቢኾን ምን ሊሠራ እንደሚችል በችግር ውስጥ ኾኖ የሠራቸው ሥራዎች አብነት እንደኾኑ አስገንዝበዋል።
የክልሉ መሪዎች ተረጋግተው፣ ሕዝቡን ከጎናቸው አሰልፈው የልማት ሥራዎችን ሠርተው ቢኾን ኖሮ ከዚህ የላቀ ይኾን እንደነበር ነው የተናገሩት።
ያመለጣችሁ ዕድል ያስቆጫል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላም ቢኾን ኖሮ የክልሉ የልማት ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ያድግ ነበር ነው ያሉት።
ክልሉ ወደ ሰላም እጦት የገባው ያለ ምክንያት አይደለም፣ የአማራ ሕዝብ በተጨባጭ ምላሽ የሚፈልግባቸው፣ ለብዙ ጊዜያት ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች እንዳሉት አውቃለሁ፤ መንግሥታችን ያውቃል፣ ለመፍታትም ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
አንዳንድ አካላት የሕዝብን ጥያቄ ቀምተው ለመፍታት አስቸጋሪ ወደ ኾነ ቦታ ቢወስዱትም አሁንም ቢኾን የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ኾኖ በጋራ ጥረት በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ ጥርጥር የለኝም ነው ያሉት። ለተግባራዊነቱም የበኩሌን ለመወጣት ቃል እገባለሁ ብለዋል።
ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ከችግሩ በፍጥነት የምንወጣበትን መንገድ ማፋጠን ከሕዝብ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ እና በሚዲያ ጦርነት የሚቀሰቅሱ ወገኖች አማራንም ኢትዮጵያንም ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛሉ ብለዋል።
እነርሱ በሚሉት መንገድ መፍትሔ የሚገኝ ቢኾን ኖሮ ሕዝቡ ለተጨማሪ ስቃይ ሳይዳረግ፣ ሃብትና ንብረት ሳይወድም መፍትሔ ያገኝ ነበር፣ ነገር ግን ባሉት መንገድ መፍትሔ አልተገኘም ነው ያሉት።
በጦርነት መፍትሔ ቢመጣ ኖሮ የእስካሁኑ ጊዜ ያመጣ ነበር፤ ነገር ግን መፍትሔ አላመጣም ሲሉ አስረድተዋል። ግጭቱ አማራ በአማራ እንዲጎተት፣ መሪ እንዲያጣ እያደረገው መኾኑንም ገልጸዋል።
ከአማራ አልፎ ለሀገር እና ለዓለም የሚበቁት መሪዎች የተቀጩት በማንም አለመኾኑን አስታውሰዋል። ድንቅ የአማራ ልጆች በአልተገባ ሁኔታ መቀጠፋቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ሕዝብ “የሞተው ወንድምሽ፣ የገደለው ባልሽ፣ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” ይሉት ተረት ደርሶበታል ነው ያሉት።
ሌሎች ክልሎች የሕዝባቸውን ልማት በሚቀይሩ የልማት ሥራዎች ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
እናንተ ብዙ ተምራችኋል፤ የሰላምን ዋጋ አውቃችኋል። የግጭትን ምዕራፍ በንግግር ዘግተን ችግር የሚፈታበትን አካሄድ እንከተል ብለዋል። በጥፋት ጎዳና ያሉትን ይብቃችሁ በማለት ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለማምጣት ርብርብ እናድርግ ነው ያሉት።
ልመና እና ተረጅነትን በማስቀረት ተግተን ሠርተን ራስን መቻል አለብን ብለዋል። ኢትዮጵያ ፋና ወጊ የኾነ አኩሪ የነጻነት ታሪክ ያላት ብትኾንም በምግብ ራሳችንን ባለመቻላችን አደጋ በሚገጥመን ጊዜ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት አቅቶን እጃችን ለእርዳታ ስለምንዘረጋ የድህነት ምሳሌ ኾነን ቆይተናል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎችም የምትተርፍበት የተፈጥሮ ሃብት አቅም እንዳላትም ተናግረዋል።
ራሳችንን መቻል ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
