
ደሴ፡ ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር” በሚል መሪ መልዕክት ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ውይይቱን የሐረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦድሪን በድሪ እና የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ መርተውታል።
የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግራቸው የደሴ ከተማ ሕዝብ ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚያከብር የመቻቻል ተምሳሌት የኾነ ሕዝብ ከመኾኑ በተጨማሪ ለከተማዋ ሰላም እና ልማት ሰፊ ተሳትፎ የሚያደርግ የነቃ ሕዝብ ነው ብለዋል።
የከተማው አሥተዳደርም የከተማዋ ነዋሪዎች የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበሩ የልማት ሥራዎችን ቃል በተገባው መሠረት ገንብቷል ነው ያሉት ።
የከተማዋ አሥተዳደር አሁንም የነዋሪዎችን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ
የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
የተማሪዎች ምገባ ተጀምሯል፣ የትምህርት እና የጤና ተቋማት፣ የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በከንቲባ ችሎት እና በሥራ አሥፈፃሚ ችሎትም ለበርካታ ዓመታት የተንከባለሉ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች መልስ እየተሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኦድሪን በድሪ እንደ ሀገር ዕዳ ለትውልድ እንዳይሻገር ብልጽግና ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
ልመና እና ተረጅነትን ማስቀረት እና ወደ ምርታማነት መሸጋገር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ደረጃ ልመና እና ተረጂነትን የሚጠየፍ አስተሳሰብ መገንባት እና ምርታማነትን በማረጋገጥም ድህነትን ለማሸነፍ እና ሉዓላዊ ክብርን ለማረጋገጥ ለሚከናወኑ ተግባራት ማኅበረሰቡ ተባባሪ በመኾን የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
በደሴ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች፣ የኮሪደር ልማት እና የመንገድ ሥራን መመልከታቸውን እና የነዋሪዎች እና የከተማ አሥተዳደሩ ቅንጅት የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ የመወያያ ጹሑፍ አቅርበዋል።
የክልሉ እና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን፣ የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ፣ እንዲሁም የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የደሴ ከተማ ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በውይይቱ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
