
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተረጅነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከባሕርዳር ከተማ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ተስፋዬ ይገዙ፣ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ሀገር፣ የብዙዎች መኖሪያ፣ ታፍራ እና ተከብራ የኖረች የገናና ታሪክ ባለቤት ናት፣ ገናና ታሪክ የጻፈችው በልጆቿ ነው፣ ልጆቿ በጀግንነት፣ በአንድነት ስለሠሩ ታሪክ ሠርተዋል ብለዋል። በታሪኩም ስንኮራ ኖረናል ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመኾን ገናና ታሪክ የሠራ ሕዝብ መኾኑን ተናግረዋል። በሀገር ላይ የሠራው ታሪክ ሲነገር እንደሚኖር ነው የገለጹት። ባለፉት ዓመታት በተሠሩት የልዩነት ዘሮች የአማራ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንደደረሰበትም ገልጸዋል።
ሌሎች ኢትዮጵያውያንም የሥርዓቱ ተጎጂ ቢኾኑም የአማራ ሕዝብ በልዩነት መጎዳቱን ነው የተናገሩት።
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዲነጠል እንደተሠራበትም አስታውሰዋል።
ለውጡ ከመጣ ወዲህ የበዳይ ተበዳይ ትርክት እንዲሻር፣ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት እንዲጠናከር እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
የአማራ ሕዝብ ችግሮቹን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት ፈትቶ በሰላም እንደሚኖር ተስፋ ይዟልም ብለዋል።
በአማራ ክልል የሰሜኑ ጦርነት ከማብቃቱ ማግሥት የውስጥ ግጭት እንዳጋጠመውም ተናግረዋል።
በተፈጠረው ግጭት የከተማዋ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ሥራዎች ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበር አንስተዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ ኀይሎች እና በሰላም ወዳዱ ሕዝብ ሰላሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉን ነው የተናገሩት።
አሁን የተጀመረው ሰላም እንዲጸና መሥራት አለብን ብለዋል።
በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የሚቀጥሉት የተጠናከረ ሰላም ሲቀጥል እንደኾነ አስረድተዋል።
በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
ለከተማዋ ነዋሪዎች ፍትሕ ለመስጠት የከንቲባ ችሎት በመጀመር በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ሰላማችንን አሟልተን፣ የልማት ሥራዎችን አፋጥነን፣ ራሳችን መቻል አለብን ነው ያሉት።
የሚለምን ሀገር ችግር እንደሚያጋጥመው አንስተዋል። ገናና ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን፣ ነገር ግን ድኾች ነን፣ ድኅነትን ሠርተን ማስወገድ አለብን ብለዋል።
የሚለምን አይከበርም፣ የሚሰጥ ግን ይከበራል ብለዋል። ከድህነት የወጣን ስንኾን አዳማጫችን እንደሚበዛ አስረድተዋል።
ተረጅነት እና የተረጅነት አስተሳሰብን እናስወግዳለን፣ ብሔራዊ ክብርንም ከፍ እናደርጋለን ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
