
ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቅርሶች የአንድ ማኅበረሰብ የታሪክ እና የማንነት አሻራ በመኾናቸው የቅርሱ ባለቤት የኾነው ሕዝብ እና መንግሥት በመጠበቅ እና በመንከባከብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሻገር ኃላፊነት አለበት።
በአማራ ክልል የሚገኙ ቅርሶችን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ባለፉት ዓመታት የጥገና እና እንክብካቤ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል። ጥገና እየተደረገላቸው ከሚገኙት ውስጥ ከባሕር ዳር ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የኡራ ኪዳነምህረት ገዳም አንዷ ናት።
በቤተክርስቲያኗ የቅርስ የጥገና እና ገንዘብ ያዥ መጋቢ ተስፉሁን ባያብል ቤተክርስቲያኗ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተች ነግረውናል። በጣና ሐይቅ ውስጥ ከሚጎበኙ ቦታዎች ውስጥ አንዷ ናት። ቤተክርስቲያኗ ላይ በጊዜ ሂደት ምክንያት ጉዳት በመድረሱ በክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በተመደበ በጀት እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በየጊዜው ጊዜያዊ ጥገናዎች ሲደረግ ቆይቷል። በ2015 ዓ.ም ብቻ ቢሮው በመደበው 900 ሺህ ብር እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የተለያዩ የጥገና ሥራዎች መሠራቱን ነው የገለጹት። በዚህ ዓመትም ባሕል እና ቱሪዝም ተጨማሪ የጥገና በጀት መመደቡን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በጉልበት እና በገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥገና ባለሙያ በፈቃዱ ተስፋየ እንዳሉት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጭ ጊዜያዊ ጥገና መደረጉን ገልጸዋል። ቢሮው የመደበውን 40 በመቶ ያህል ብር ደግሞ ማኅበረሰቡ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል። ቤተ ክርስቲያኗ በእንጨት፣ ድንጋይ እና ጭቃ የተሠራች በመኾኗ የጥገና ሥራውን በማኅበረሰቡ ጉልበት እና ቁሳቁስ ጭምር ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመትም 1 ሚሊዮን 500 ብር መመደቡን ነግረውናል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻየ መለሰ እንዳሉት ደግሞ በክልሉ የሕልውና አደጋ የተደቀነባቸውን 38 ቅርሶችን የቅርስ ጥገና፣ እንክብካቤ እና የሙዚየም ግንባታ ሥራ ለመሥራት 74 ሚሊዮን ብር ተመድቧል። የጥገና እና እንክብካቤ ሥራ ከሚሠራባቸው ውስጥ ዘጠኙ በአዲስ ሲኾኑ ሰባቱ ደግሞ የሙዚየሞች ግንባታዎች ናቸው።
የቅርሶች የጥገና ሂደትም የተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲኾን በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁ እንደሚኖሩ ገልጸዋል። ለቅርሶች የሚመደበው በጀት መሻሻሎች ቢኖሩም ከሚጠገኑት ቅርሶች መጠን አኳያ ሲታይ ግን ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተጠይቆ 74 ሚሊዮን ብር መመደቡ ለቅርሶች ጥገና የሚመደበው በጀት ዝቅተኛ መኾኑን በማሳያነት አንስተዋል።
ክልሉ ከፍተኛ የቅርስ ሃብት ባለቤት ቢኾንም ቅርሶቹ የሚገኙባቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ችግር ያለበት በመኾኑ ለመለየት አስቸግሯል። በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተጀመሩ ቅርሶችን ጥገና ተከታትሎ በወቅቱ ለማጠናቀቅ አለመቻሉን አንስተዋል። ማኅበረሰቡ ቅርሶችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!