
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ ከተማ ነዋሪዎች ሰላምን ለማምጣት ዓላማ ያደረገ ውይይት ከዞኑ ኮማንድ ፖስት እና ከክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ጋር አድርገዋል። ባለፉት 10 ወራት በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በማርገብ ሰላምን ለማምጣት የክልሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ከሕዝቡ ጋር እየመከሩ ነው።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ ከተማ ነዋሪዎችም ሰላምን ለማምጣት ዓላማ ያደረገ ከዞኑ ኮማንድ ፖስት፣ ከክልሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ከሕዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ የተገኙት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ሕዝቡ እና የጸጥታ አካላት በቅንጅት ያመጡት አንፃራዊ ሰላም ወደ ኋላ እንዳይመለስ በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከደብረ ወርቅ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የመከሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ የተከሰተው ግጭት ለዓመታት ሊተካ የማይችል ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማስከተሉን አንስተዋል።
ዶክተር ድረስ “በግጭቱ ምክንያት በክልሉ የደረሰውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ለማስወገድ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት ቀዳሚ አማራጭ ሊኾን ይገባል” ብለዋል። በውይይቱ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሠብሣቢ አስቻለ አላምሬ አለመግባባቶች በእርቅ እና በንግግር እንዲፈቱ ነፍጥ አንስተው ወደ ጫካ የገቡ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመለሱ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰዋል። ለተፈፃሚነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ነው የጠየቁት።
በምዕራብ እዝ የ403 ኮር አዛዥ እና የምሥራቅ ጎጀም ዞን ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ብ/ጀኔራል አዘዘው መኮንን እርስ በእርስ በመገዳደል ሰላምን ማምጣት አይቻልም ነው ያሉት። ሁሉም ልቡን ለንግግር፣ ለይቅርታ እና ለሰላም ክፍት ያድርግ ብለዋል።
በውይይቱ ሃሳባቸውን የሰጡ የደብረወርቅ ከተማ ነዋሪዎች የሕዝቡ ስቃይ ሊበቃ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሕግ እና ሥርዓትም እንዲከበር ጠይቀዋል። ሰላም እንዲመጣ የድርሻቸውን ለመወጣትም ዝግጁ መኾናቸውንም አሳይተዋል።
በመድረኩ በአካባቢው እየታየ ያለው አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ ክልላዊ እና ሀገራዊ አንድነትን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!