
ደሴ: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ኦርዲን በድሪ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ እና የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች በደሴ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከሌሎች የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች ጋር በመኾን የተሠሩ እና በመሠራት ላይ ያሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን አስጎብኝተዋል።
መሪዎቹ በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ እየተሠራ የሚገኘውን የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የመናኸሪያ አገልግሎት የግንባታ ሥራ እና በቅርቡ እድሳት የተደረገለት የከተማ አሥተዳደሩ ሕንፃ የጉብኝታቸው መዳረሻ ነው። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በደሴ ከተማ የነበረውን ከፍተኛ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የፈታውን የከንቲባ ችሎት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለሥራ ኀላፊዎቹ ሰጥተዋል።
መሪዎቹ የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን በመግለጽ ያላለቁ የልማት ሥራዎች በጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!