
ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማስተሳሰር ለአህጉሪቷ ነጻ የንግድ ቀጣና መሳለጥ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል። የአፍሪካ ኅብረት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መጋቢት/2018 በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ባካሄደው የመሪዎች ጉባኤ የተሳተፉ 44 የአፍሪካ ሀገሮች የአህጉሪቷን ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ስምምነቱም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 1 ቀን 2021 ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገ ሲኾን፤ ኢትዮጵያ በአየር መንገዷ በኩል በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የሚጓጓዘውን የመጀመሪያ ጭነት ከኤስዋቲኒ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት እንዲጀመር አድርጋለች፡፡ ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግም በ2034 በአፍሪካ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ60 በመቶ በማሳደግ በመካከላቸው ያለውን የሸቀጦች የንግድ ታሪፍ 90 በመቶ እንደሚያስቀርም ነው የሚገለጸው፡፡
የ3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ዓመታዊ ምርት ድረሻ እንደሚኖረውም ተነግሯል፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጣና ውጤታማነት የአየር ትራንስፖርት ትስስር ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል። በአህጉሪቷ መካከል ያለውን የሰዎች እንዲሁም የሸቀጦች ማጓጓዝን በማሳለጥ ተመጋጋቢ የኾነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ሚናው ከፍተኛ ስለመኾኑ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አህጉሪቷን በማስተሳሰር የአፍሪካ መሪዎች የወጠኑትን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ውጤታማነት ሚናውን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡ አየር መንገዱ በአፍሪካ ያሉትን መዳረሻዎች እያሳደገ ሲኾን በአሁኑ ወቅት 64 የአፍሪካ ከተሞች ላይ እንደሚበር ገልጸዋል። ይህም አየር መንገዱ አብዛኛውን የአፍሪካን ሀገራት በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ተግባሩን እያፋጠነ መኾኑ ማሳያ ነው ብለዋል። በጥቂት ጊዜ ውስጥም አየር መንገዱ የቀሩትን ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት በአየር ትራንስፖርት የማስተሳሰር ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
ኢዜአ እንደዘገበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 147 በላይ አውሮፕላኖቹ 136 ዓለም አቀፍ እና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!